ቀጥታ፡

ብልጽግና ፓርቲ በሐረሪ ክልል የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰው ተኮር ተግባራት አከናውኗል

ሐረር ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ በሐረሪ ክልል የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰው ተኮር ተግባራት አከናውኗል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

ብልጽግና ፓርቲ በሐረሪ ክልል ለህዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ ዕጩዎቹን የማስተዋወቅና የምረጡኝ ቅስቀሳውን በሐረር ከተማ አካሂዷል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪን ጨምሮ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና የአካባቢው ማህበረሰብ ተገኝተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢትዮጵያ የልማትና እድገት አቅጣጫ ትክክለኛ መሰረት የያዘበትና ዘርፈ ብዙ ውጤቶች የተገኙት በብልጽግና ፓርቲ ትጋትና ቁርጠኝነት መሆኑን አንስተዋል።

በሐረሪ ክልል የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰው ተኮር ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።

በለውጡ አመታት በፓርቲው መሪነት በገጠርም ይሁን በከተሞች ሁሉን አቀፍ የልማት ስራዎች መሰራታቸውንም አስረድተዋል።

የዓለም ቅርስ የሆነው ጀጎል መልሶ ማልማት እና የሐረር ውብ የኮሪደር ልማት ስራዎች እንዲሁም ሌሎች ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ተጨባጭ ስራዎች የተከናወኑበት መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ለልማት፣ ለዴሞክራሲ ግንባታ፣ ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ብሎም ለሀገር እድገት ብልጽግናን መምረጥ መቻል ትክክለኛ ውሳኔ ይሆናል ብለዋል።


 

በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ጌቱ ወየሳ፤ ብልፅግና ፓርቲ የሀገር ልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ መሰረት ያኖረ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

በመሆኑም ይህንን መልካም ጅምር ለማስቀጠል ፓርቲው የተሟላ አቅም ያካበተ መሆኑን አንስተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም