ከፓን አፍሪካኒዝም እስከ ኢኮኖሚያዊ አጋርነት - የኢትዮጵያ እና ብሩንዲ የስድስት አስርት ዓመታት የዲፕሎማሲ ጉዞ - ኢዜአ አማርኛ
ከፓን አፍሪካኒዝም እስከ ኢኮኖሚያዊ አጋርነት - የኢትዮጵያ እና ብሩንዲ የስድስት አስርት ዓመታት የዲፕሎማሲ ጉዞ
በሙሴ መለሰ
የኢትዮጵያና የብሩንዲ ግንኙነት የሚጀምረው አፍሪካ ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ለመውጣት በምትታገልበት ወሳኝ ወቅት እንደነበረ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት እንደመሆኗ፣ ብሩንዲ እ.ኤ.አ በ1962 ከቤልጂየም ቅኝ አገዛዝ ወጥታ ነፃነቷን ስታገኝ ግንኙነታቸውን በይፋ ከጀመሩ የመጀመሪያዎቹ አገራት ተርታ ትመደባለች።
ይህ ግንኙነት በወቅቱ በነበረው የፓን-አፍሪካዊነት መንፈስ እና አፍሪካዊ መፍትሄ ለአፍሪካዊ ችግሮች በሚለው መርህ ላይ የቆመ ነበር።
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) ምስረታ ላይ የነበራቸው የጋራ ተሳትፎ ለዘመናት ለዘለቀው ወንድማማችነት ጠንካራ የመሰረት ድንጋይ አስቀምጧል።
ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አዳዲስ ከቅኝ ግዛት ነፃ የሚወጡ የአፍሪካ ሀገራትን ወደ አህጉራዊው መድረክ ለማምጣት በነበራቸው ራዕይ መሰረት፣ ከብሩንዲ የመጀመሪያው ንጉሥ ምዋሚ ምዋቡትሳ አራተኛ ጋር የጠበቀ ግንኙነት መስርተዋል።
ግንኙነቱ በይፋ ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላም (እ.አ.አ 1963) ብሩንዲ በአዲስ አበባ በተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት) ላይ በመስራች አባልነት እንድትሳተፍ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጋለች።
በወቅቱ የነበረው የሀገራቱ ግንኙነት በፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል እና በቀጣናዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ነበር።
በወቅቱ ይደረጉ በነበሩ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብስባዎች ላይ ኢትዮጵያ እና ብሩንዲ አህጉራዊ አጀንዳዎችን በጋራ አንጸባርቀዋል።
ኢትዮጵያ በብሩንዲ የሰላም ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውታለች። በተለይም በብሩንዲ የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም በተደረገው ጥረት እና በአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ (AMIB) ውስጥ የኢትዮጵያ ሰራዊት ቀዳሚ ተሳትፎ ነበረው።
ልዑኩ በአፍሪካ ህብረት ታሪክ የመጀመሪያው ሙሉ በሙሉ በአህጉሪቱ የተመራና የተደራጀ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እንደሆነ ይወሳል።
ኢትዮጵያ ከደቡብ አፍሪካ እና ከሞዛምቢክ ጋር በመሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰራዊት ልካለች።
ሰራዊቱ የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲከበር ማድረግ፣ ታጣቂዎችን ትጥቅ ማስፈታት እና ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ (DDR) ላይ ትልቅ ስራ ሰርቷል።
ኢትዮጵያ በወታደራዊ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በዲፕሎማሲው ረገድም ንቁ ተሳትፎ አድርጋለች።
የአሩሻ የሰላም ስምምነት እንዲሳካ እና በብሩንዲ የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት በወቅቱ የነበሩ የኢትዮጵያ መሪዎች በኢጋድ (IGAD) እና በአፍሪካ ህብረት በኩል ጫና ሲያደርጉና ሲያሸማግሉ ቆይተዋል።
በብሩንዲ በተለያዩ ቡድኖች መካከል እምነት እንዲገነባ ኢትዮጵያ እንደ ገለልተኛ እና ታማኝ አደራዳሪ ትታይ ነበር።
ተልዕኮው ስራውን አጠናቆ ወደ ተባበሩት መንግስታት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ (ONUB) ሲቀየርም የኢትዮጵያ ሰራዊት እዛው በመቆየት ለሰላሙ ዘላቂነት አስተዋፅኦ ማድረጉን ቀጥሏል። ይህም ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ሰላም ያላትን ቁርጠኝነት አሳይቷል።
ይህም በሁለቱ ሀገራት ትብብር ውስጥ በትልቁ የሚነሳ እና የሚወሳ ነው።
በፓን አፍሪካኒዝም እና በፖለቲካዊ ወዳጅነት ላይ መሰረት አድርጎ የተጀመረው የሀገራቱ ወዳጅነት ወደ ተለያዩ መስኮች እየሰፋ መጥቷል።
እ.አ.አ በ1970ዎቹ መጀመሪያ በሀገራቱ መካከል የተፈረሙ የንግድ እና የባህልን ትብብር የማጠናከር የጋራ መግባቢያ ሰነዶች የዚሁ ማሳያ ናቸው።
ባለፉት ዓመታት በሀገራቱ መካከል የተደረጉ የጉብኝት ልውውጦች እና የጋራ ስብሰባዎች ግንኙነቱን ከማጠናከር ባለፈ የትብብር አድማሱን ማስፋትን ከግምት ውስጥ ያስገቡ መሆናቸውን ማየት ይቻላል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እ.አ.አ በ2023 በብሩንዲ ይፋዊ የስራ ጉብኝት አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከብሩንዲ ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
ውይይቱ በኢትዮጵያ እና ብሩንዲ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ ግብርና፣ አቪዬሽን እና ቀጣናዊ ሰላም ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ ነው።
በጉብኝቱ ወቅት ብሩንዲ የኢትዮጵያን የስንዴ ልማት እና የአረንጓዴ አሻራ ተሞክሮ በስፋት ለመተግበር ያላትን ፍላጎት አሳይታለች።
የሁለትዮሽ ውይይቱ የተለያዩ ውጤቶች የተገኙበት ነው።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የንግድ ልውውጥን የሚያቀላጥፉ ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ ውሳኔ ተላልፏል። ኢትዮጵያ ለብሩንዲ በቴክኒክ እና በሙያ ስልጠና (TVET) ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች።
የሀገራቱ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን (JMC) በየጊዜው እየተገናኘ ስምምነቶችን እንዲከታተል መመሪያ ተሰጥቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከውይይቱ በተጨማሪ ግብርና እና ኢንዱስትሪን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2023ቱ የብሩንዲ ጉብኝት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በማጠናከር ረገድ በዋና ማሳያነት የሚጠቀስ ነው።
የብሩንዲ ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ እ.አ.አ በ2021 በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋርም ተወያይተዋል።
በጉብኝቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለብሩንዲ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኞችን በስጦታ አበርክተው ነበር። ይህም ሀገራቱ በግብርና እና አረንጓዴ ልማት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ያላችውን ፍላጎት የሚያሳይ ነበር።
በፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ወቅት የመጀመሪያ የኢትዮ-ብሩንዲ የመጀመሪያ የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብስባ ተደርጓል።
በወቅቱ በግብርና፣ በቱሪዝም እና በትምህርት ዘርፍ አዳዲስ የመግባቢያ ሰነዶች ተፈርመዋል።
እ.አ.አ በ2023 የብሩንዲ ፓርላማ የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን (CFA) በህግ አፀደቀ (Ratified)፤ ይህም ለኢትዮጵያ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ ተቆጠረ። ኢትዮጵያ ብሩንዲ ስምምነቱን እንድታጸድቅ ድጋፍ አድርጋለች።
ይህም የሀገራቱን የውሃ ትብብር የበለጠ ያጸና ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በየካቲት ወር 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተካሄደው 39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከብሩንዲ ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል።
የቀድሞው የብሩንዲ ፕሬዝዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ እ.አ.አ በ2012 በኢትዮጵያ ጉብኝት አድርገዋል። ይህም በሀገራቱ የከፍተኛ አመራሮች የጉብኝት ልውውጦች ውስጥ የሚጠቀስ ነው።
ከንኩሩንዚዛ ጉብኝት ሁለት ዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ2014 ብሩንዲ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ከፍታለች። ይህም የሀገራቱን ትብብር ለማጠናከር የተወሰደ ትልቅ እርምጃ ነው።
ኢትዮጵያ ከብሩንዲ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ስራ የሚሸፍነው በካምፓላ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ነው።
ኢትዮጵያ እና ብሩንዲ በተለያዩ ጊዜያት ተደራራቢ ታክስን ማስቀረት፣ በኢንቨስትመንት፣ አየር ትራንስፖርት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በመከላከያ እና ፀጥታ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲሁም ባህልና ስፖርት ትብብራቸውን ለማጠናከር የሚያስችሉ ስምምነቶች ተፈራርመዋል።
ጉብኝቶችና ስምምነቶች ኢትዮጵያና ብሩንዲ ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ትብብር በማሳለጥ እና የጋራ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ረገድ ያላቸው ሚና ወሳኝ ነው።
ሁለተኛው የኢትዮጵያና የብሩንዲ የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽን (Joint Ministerial Commission - JMC) መጋቢት 29 እና 30 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
ስብስባውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) እና የውጭ ጉዳይ፣ የቀጣናዊ ትስስርና የልማት ትብብር ሚኒስትር አምባሳደር ኤድዋርድ ቢዚማና በጋራ መርተውታል።
በተጨማሪም የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና የዘርፍ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
በስብስባው ማብቂያ የተለያዩ የሁለትዮሽ ስምምነቶች ተፈርመዋል።
ስምምነቶቹም በዋናነት በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር (በተለይም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ)፣ በግብርና ምርታማነት፣ በአቪዬሽን እና በቀጣናዊ ደህንነት ዙሪያ ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ስብስባው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠናን (AfCFTA) መርህ መሰረት በማድረግ የሁለቱን ሀገራት የኢኮኖሚ ትስስር ማጠናከር፣ የመሰረተ ልማት ግንኙነቶችን ማስፋፋት እና በአባይ ተፋሰስ የጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ተቀራርቦ ለመስራት የሚያስችል የጋራ መግባቢያ ሰነድ በመፈረም በስኬት ተጠናቋል።
ውይይቱ የኢትዮጵያ እና የብሩንዲን ትብብር የበለጠ ማጠናከር የሚያስችል ነው።
የቡሩንዲ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ኤቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ፕሬዝዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ ጉዳዮች ላይ ውይይቶችን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኤቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው የሁለቱን ሀገራት ትብብር ከማጠናከር ባለፈ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ትስስር ይበልጥ የሚያጎለብት ነው።
የኢትዮጵያ እና የብሩንዲ መጻኢ የሁለትዮሽ ትብብር በሁለገብ ዘርፎች ላይ ያተኮረና ወደ ላቀ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የሚሸጋገርበት ወቅት እንደሚሆን ይጠበቃል።
የፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንዳይሺሚዬ ጉብኝት እና የጋራ ሚኒስትሮች ኮሚሽኑ ውሳኔዎች፣ ለቀጣዮቹ ዓመታት በሁለቱ ሀገራት መካከል ለሚኖረው ጠንካራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ትስስር መጠናከር ጉልህ ሚና ይኖረዋል።