ቀጥታ፡

ኢትዮ ቴሌኮም "ቶሎ" የተሰኘ የፈጣን መንገድ የክፍያ ሥርዓትን በቴሌ ብር ማከናወን የሚያስችል ዲጂታል የክፍያ ስርዓት አስጀመረ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮ ቴሌኮም "ቶሎ" የተሰኘ የፈጣን መንገድ የክፍያ ሥርዓትን በቴሌ ብር አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን ዲጂታል የክፍያ ስርዓት አስጀመረ።

ኢትዮ ቴሌኮም "ቶሎ" የተሰኘ የፈጣን መንገድ የክፍያ ሥርዓትን በቴሌ ብር ማከናወን የሚያስችለውን ዲጂታል የክፍያ ስርዓት የማስጀመር መርሀ ግብር በቱሉ ዲምቱ ዋና የክፍያ ጣቢያ እያካሄደ ነው።

የክፍያ ስርዓቱን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እና የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሙስጠፋ አባሲመል በቱሉ ዲምቱ ዋና የክፍያ ጣቢያ  አስጀምረዋል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ ተቋሙ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ አገልግሎቶችን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል። 


 

ኢትዮ-ቴሌኮም ከመደበኛ የቴሌኮም አገልግሎት ባሻገር ቀልጣፋ፣ ምቹና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት በማቅረብ የፋይናንስ ዘርፉን እየደገፈ መሆኑንም አስረድተዋል። 

በዚህም የሀገርን ልማት ዘላቂና አካታች ለማድረግ የዲጂታል መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ ትኩረት በማድረግ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል።

ዛሬ የተጀመረው አገልግሎት የትራንስፖርት ዘርፉ በተሻለ ደረጃ አገልግሎት እንዲሰጥ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ይህም ደንበኞች ለዚሁ ዓላማ የተዘጋጀ ካርድ ተጠቅመው ክፍያ እንዲፈጽሙ የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሙስጠፋ አባሲመል በበኩላቸው፤ ካሁን ቀደም ወረቀትን መሰረት ያደረገ ክፍያ ስርዓት ይከናወን እንደነበር ገልፀዋል።


 

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ ማስደገፍ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተው፤ አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ የማድረግ ጉዞ ዛሬ መጀመሩን ይፋ አድርገዋል።

"ቶሎ" የተሰኘ የክፍያ ስርዓት ሶፍትዌር መልማቱን አመልክተው፤ በዚህም ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር ከቴሌ ብር ጋር በማስተሳሰር ዘመናዊ የክፍያ ስርዓት መጀመሩን አብስረዋል።


 

በዚህም ደንበኞች የተዘጋጀ ካርድ በመጠቀም ክፍያ እንዲፈፅሙ በማስቻል ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚያገኙ ተናግረዋል።

ሁለቱ ተቋማት በቀጣይ አብሮ መስራት የሚያስችል የፊርማ ስምምነት ስነ-ስርአትም አካሂደዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም