ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ተከናወነ

ባህርዳር ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በባህር ዳር ከተማ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ300 አቅመ ደካማ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ተከናወነ።

‎‎የባህር ዳር ከተማ የበጎ አድራጎት ማህበር በከተማዋ ለሚገኙ 300 አቅመ ደካማ ወገኖች የትንሳኤ በዓልን ምክንያት ያደረገ ማዕድ አጋርቷል።

‎የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ አህመድ ይማም ማዕድ ባጋሩበት ወቅት እንደገለፁት ማህበሩ በዓል ሲመጣ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የበዓል መዋያ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።


 

‎‎ዛሬም የትንሳኤ በዓልን አስመልክቶ በባህርዳር ከተማ በሶስት ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ 300 አቅመ ደካማ ወገኖች የገንዘብና የዶሮ ድጋፍ ማድረጉን ገልፀዋል።

‎‎እንዲሁም በፋና የበጎ አድራጎት ማህበር ለታቀፉ አቅመ ደካማ ወገኖች አንድ የበሬ ሰንጋ ለበዓል መዋያ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል። 

‎‎‎የፋሲሎ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ገረመው አባተ በበኩላቸው፤ በጎ አድራጎት ማህበሩ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ አቅመ ደካማ ወገኖች እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።


 

‎ማህበሩ ከ3 ሺህ 300 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካማ ወገኖች በየዓመቱ የጤና መድህን ወጪን በመሸፈን ጤናቸውን እንዲጠብቁ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝም ተመልክቷል።

‎‎የጣና ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ የሺኢትዮጵያ መኮነን የተደረገው ድጋፍ በዓሉን ከቤተሰባቸው ጋር ተደስተው እንዲያሳልፉ ምክንያት ይሆናል ብለዋል።

‎‎የፋሲሎ ክፍለ ከተማ ነዋሪ እማሆይ ማንአህሎሽ ደርሶ በበኩላቸው፤ በጎ አድራጎት ማህበሩ በዓል በመጣ ቁጥር የዶሮና የዘይት ድጋፍ ስለሚያደርግልን በዓሉን ሳንቸገር እንድናሳልፍ ረድቶናል ብለዋል።


 

‎‎በተጨማሪም በየዓመቱ የጤና መድህን ወጪያቸውን በመሸፈን ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ እያገዛቸው እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም