ቀጥታ፡

በመዲናዋ ለትንሳኤ በዓል የሚቀርቡ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዳይቆራረጡ ዝግጅት ተጠናቋል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦በትንሳኤ በዓል ወቅት በመዲናዋ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ እንዳያጋጥም እና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች በውጤታማነት እንዲሰጡ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ጽህፈት ከተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን ለትንሳዔ  በዓል የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ቅድመ ስራዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ስራ አስኪያጅ ይመኙሻል ታደሰ፤ በበዓል ሰሞን የሚኖረውን ከፍተኛ የፍጆታና የአገልግሎት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ የተቀናጀ እቅድ ወጥቶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

በዚህም የትንሳዔ በዓልን ያለምንም ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች መቆራረጥ ማክበር የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን አመላክተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮማንደር አሕመድ መሐመድ በበኩላቸው፤ በበዓል ወቅት አደጋዎች እንዳይከሰቱ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።


 

ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር ለእሳት አደጋ መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉ ነገሮች ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባው ጠቅሰው፤ አደጋዎች ከተከሰቱ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ በሰው ሃይልና በግብዓት ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ምክትል ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ጂሳ ካሳ፤ በበዓሉ ወቅት አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት እንዲኖር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።


 

ምን አልባት የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ካጋጠመ ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ የቴክኒክ ባለሙያዎች 24 ሰዓት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የውሃ ደንበኞች አገልግሎት ዳይሬክተር ሃይለየሱስ ደህናነው፤ ለበዓሉ በተለይ የውሃ መስመሮችን በመፈተሽ ጥገና ለሚያስፈልጋቸው ጥገና በማከናወን ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል። 


 

በበዓሉ ወቅት የሚመነጩ ልዩ ልዩ ቆሻሻዎችን ለማንሳት የሽርክና ማህበራት ተሽከርካሪዎች ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሳዲቅ ሽኩር ናቸው።


 

ህብረተሰቡም ለከተማዋ ጽዳት ልዩ ልዩ ተረፈ ምርቶችን በአግባቡ በመያዝ ለሚመለከታቸው ሽርክና ማህበራት ማስረከብ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም