የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ፍትሐዊና ለቀጣናው መረጋጋት ወሳኝ ነው ሲሉ የአውሮፓ ፓርላማ አባል ቲየሪ ማሪያኒ ገለፁ።
በአራተኛው ዓመታዊ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የቀይ ባሕር እና የኤደን ባህረ ሰላጤ ውይይት ላይ የታደሙት የአውሮፓ ፓርላማ አባል ቲየሪ ማሪያኒ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከፍትሃዊነት ባለፈ ለዓለም አቀፍ ደህንነት ሚናው የጎላ ነው።
እንደ ባብ ኤል-መንደብ ያሉ ጠባብ የባህር መተላለፊያዎች መዘጋት በአውሮፓ የነዳጅ እና የማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይገኛሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ስትራቴጂካዊ ቀጣና ውስጥ የምትገኝ ቁልፍ ሀገር በመሆኗ ያላት ሚና ለዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በባህር ሕግ ስምምነት ላይ እያንዳንዱ ሀገር የባህር በር ሊኖረው እንደሚገባ በግልጽ መቀመጡንም አንስተዋል።
አውሮፓ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲኖር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት የገለጹት የአውሮፓ ፓርላማ አባል ቲየሪ ማሪያኒ፤ ለዚህም የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ይህም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው መረጋጋትና ለዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ደህንነት ዋስትና እንደሚሆን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት አንዷ እና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ ሆና የባህር በር አልባ መሆኗ አመክንዮአዊ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።