የነዳጅ ስርጭትና አጠቃቀም ላይ የተቀመጠው አሰራር ከዚህ ቀደም ያጋጥሙ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የቀረፈ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የነዳጅ ስርጭትና አጠቃቀም ላይ የተቀመጠው አሰራር ከዚህ ቀደም ያጋጥሙ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የቀረፈ ነው
ሃዋሳ ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦የነዳጅ ስርጭትና አጠቃቀም ላይ የተቀመጠው አሰራር ቀልጣፋ እና ከዚህ ቀደም ያጋጥሙ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የቀረፈ መሆኑ ተመለከተ፡፡
በሀዋሳ ከተማ የነዳጅ ስርጭትና አጠቃቀም በተቀመጠው አሰራርና የመፍትሄ አቅጣጫ መሰረት እየተከናወነ መሆኑንም የከተማ አስተዳደሩ የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታውቋል።
በመካከለኛው ምስራቅ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት በኢትዮጵያ የነዳጅ ግብይትና አቅርቦት ላይ የሚያጋጥመውን ችግር ለመሻገር መንግስት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡
የሃዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባና የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ አገና ኔቶ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እንደ ሃገር ነዳጅን በቁጠባ በመጠቀም ፍትሀዊ ስርጭቱን ለማረጋገጥ ቅድሚያ ነዳጅ እንዲያገኙ ለተፈቀደላቸው ተሽከርካሪዎች በኩፓን እንዲገበያዩ ተደርጓል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ፍትሃዊ የነዳጅ ስርጭትና ቁጥጥር ለመተግበር ግብረ ሃይል አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱንም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ነዳጅ ለሚያመላልሱ ቦቴዎች፣ የኤክስፖርት ምርቶች ለጫኑ ካሚዮኖች፣ ለአምራች ኢንዱስትሪዎችና ለህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ በመስጠት እንዲስተናገዱ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ግብረ ሃይሉ እጥረቱን ተከትሎ ነዳጅ ላልተገባ ተግባር እንዳይውል ባደረገው ክትትልና ቁጥጥር በ17 ተሸከርካሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱንም ተናግረዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እያከናወነ ያለው ተግባር ውጤት እየታየበት እንደሆነም ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
በከተማው ነዳጅ የሚያቀርቡ ማደያዎችም የተቀመጠውን መመሪያ ተከትለው እየሰሩ በመሆናቸው ከዚህ ቀደም የነበሩ ሰልፎች አለመኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
የሃበሻ ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅ አቶ አባይ በሪሁን በበኩላቸው ከመንግስት በወረደው የአሰራር መመሪያ መሰረት ቅድሚያ ለሚሰጣቸውና ከሚመለከተው አካል ኩፖን ይዘው ለመጡ ተሸከርካሪዎች ነዳጅ በፍጥነት ማስተናገዳቸውን ተናግረዋል፡፡
አሰራሩ ቀልጣፋና ከዚህ ቀደም ያጋጥሙ የነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን የቀረፈ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ነዳጅን በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሲቀዱ ያገኘናቸው አሽከርካሪዎች እንዳሉት፤ አዲሱ አሰራር ከዚህ ቀደም በነዳጅ ማደያ ቆመው የሚያጠፉትን ጊዜ አስቀርቶላቸዋል፡፡
አሰራሩ ቀጣይነት እንዲኖረው ክትትሉ መጠናከር እንዳለበትና ያገኙትን ነዳጅ ቆጥበው በመጠቀም ያጋጠመውን የነዳጅ እጥረት ለመሻገር የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡