የለውጡ ዓመታት ድንቅ የብልፅግና ውጤቶች የተመዘገቡበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የለውጡ ዓመታት ድንቅ የብልፅግና ውጤቶች የተመዘገቡበት ነው
ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦ ያለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያን ከጨለማ ወደ ብርሃን ማሻገር ያስቻሉ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።
መጋቢት 24 የመጣውን ለውጥና የለውጡን የ8 ዓመታት ትሩፋቶችና ውጤቶችን የሚዘክር ታላቅ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ በድሬዳዋ ተካሂዷል።
ከንቲባ ከድር ጁሃር ለገሃር አደባባይ ለተሰበሰቡት የድጋፍ ሰልፈኞች ባስተላለፉት መልዕክት፤ ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያን ከጨለማ ወደ ብርሃን ያሻገሩ ድንቅ ሀገራዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በተለይም አሰባሳቢ የወል ትርክትን በማንበር ከመራራቅ ወደ ህብረ ብሔራዊ የአንድነት ፅናት በመሻገር ታላቅ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
መጋቢት 24 የለውጡን የድል ቀን ተከትሎ በመላው ሀገሪቱና በድሬዳዋ አስተዳደር በተከናወኑ ታላላቅ የልማት ስራዎች ከልመና ወደ ምርታማነት የሚሸጋገርና ተረጂነትን የሚጠየፍ ትውልድ መገንባት እያስቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ለውጡ አጋርነትና ዋና የተባለ አግላይ አካሄድ መቀየሩ በፀና የአመራር ቅንጅት በድሬዳዋ አስተዳደር በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚው እና በፖለቲካው ታላቅ ውጤቶች ለማስመዝገብ ማስቻሉን አስረድተዋል።
በለውጡ ዓመታት በአስተዳደሩ የገጠር ቀበሌዎች ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና እየተረጋገጠ ይገኛል ያሉት ከንቲባ ከድር፤ በከተማም ድሬዳዋን በኮሪደር ልማት ውብ የስራና የመኖሪያ ማዕከል በማድረግ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ፍሰት እንዲጨምር ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
እነዚህ የለውጥ ትሩፋቶች እና ውጤቶች ከህዝብ ፍላጎት አንፃር ሲመዘኑ ብዙ ርቀት መጓዝ ያስፈልጋል ያሉት ከንቲባው፤ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሰው ተኮር ልማቶች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ድሬደዋ የህዝብን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ድንቅ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ውጤቶች በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል የሁሉም አካላት ርብርብ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የመጋቢት 24 ትሩፋቶች ከኢትዮጵያ ትንሳኤና ከህዝባችን መሻት ጋር አስተሳስሮ መመልከት ይገባል ያሉት አቶ ኢብራሂም፤ በለውጡ ዓመታት የተገኙ ውጤቶችንና ድሎችን በመጠበቅና በማስፋት ልዕልናዋን ያረጋገጠች ሀገር ለትውልድ ማውረስ እንችላለን ብለዋል።
ዛሬ በተካሄደው ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች፣ ኡጋዝና አባገዳዎች እንዲሁም የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡