ቀጥታ፡

በክልሉ ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠት ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል

ባህርዳር ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የዲጂታል አገልግሎቶችን በማስፋት ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት የመስጠትና ብልሹ አሰራሮችን የመከላከል ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን መሀመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

በአማራ ክልል የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት፣ ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያና የኢትዮ ኮደርስ አፈጻጸም ያለበትን ሁኔታ የሚገመግም መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አሕመዲን መሀመድ (ዶ/ር)፤ በክልሉ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተመረጡ ከተሞች ተጀምሮ ለሌሎች አካባቢዎችም ሞዴል በሚሆን መልኩ እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።

የፋይዳ የዲጂታል መታወቂያና የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን ተደራሽ በማድረግ ረገድም ጥሩ አፈፃፀም መመዝገቡን ገልጸዋል።

በክልሉ እስካሁን 5 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መውሰዳቸውንም ለአብነት ጠቅሰዋል።

እነዚህ አገልግሎቶች ተግባራዊ መደረጋቸው ለዜጎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል አስችሏል ብለዋል።

በቀጣይም አገልግሎቶቹን ተደራሽነት የማስፋት ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

በመድረኩ ላይ በክልሉ የሚገኙ ዘርፉን የሚመሩ የተለያዩ የቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም