መጋቢት 24 ኢትዮጵያውያንን በጋራ ያቀፈና ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ምዕራፍ የከፈተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መጋቢት 24 ኢትዮጵያውያንን በጋራ ያቀፈና ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ምዕራፍ የከፈተ ነው
ሰመራ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦ መጋቢት 24 ኢትዮጵያውያንን በጋራ ያቀፈና ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኀላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ተናገሩ።
በለውጡ የተገኙ ድሎችና ስኬቶችን ለማስቀጠል ያለመ ታላቅ የማጠቃለያ የድጋፍ ሰልፍ በዛሬው ዕለት በሰመራ ከተማ ተካሂዷል።
በሠመራ ስታዲየም በተዘጋጀው በዚሁ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የአፋር ክልል ከፍተኛ የስራ ኀላፊዎች፣ የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ነዋሪዎች፣ የመንግስት ሰራተኞችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
በሰልፉ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በብልፅግና ፓርቲ የአፋር ክልል ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኀላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን መጋቢት 24 ኢትዮጵያውያንን በጋራ ያቀፈና ለአሰባሳቢ ትርክት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ብለዋል።
የለውጡ ዓመታት አጋርነት የሚለው ቃል ቀርቶ እኩልነት የተረጋገጠበትና እውነተኛ ውህደት የታየበት በመሆኑ የአፋር ህዝብ በሀገሩ ጉዳይ ውሳኔ መስጠትና የመምራት እድል ያገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።
ብሔር ብሔሰቦችና ህዝቦች አንድነታቸውን ከፍ በማድረግ ለጋራ ዕድገት መሰባሰብ የቻሉበትና በእነዚህ ዓመታት የተመሠከሩ የልማት ውጤቶች የተመዘገቡበት መሆኑንም ተናግረዋል።
በተለይም በአፋር ክልል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ የመጣና ከዚህ ቀደም ማልማት እየተቻለ ጸጋዎች ሁሉ የተዘነጉበት መሆኑን ገልጸው፤ አሁን በክልሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በክልሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ድሎች በመምጣታቸው በየደረጃው ተጠቃሚነት ማደጉን አውስተው ይህም የመደመር መንግስት ውጤት ነው ብለዋል።
7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህዝቡ ተሳትፎውን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።
የሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱ ሙሳ በበኩላቸው፤ የለውጡ መንግስት አዳዲስ ትልሞችንና አሰራሮችን የዘረጋና ልማትን ያስቀደመ ነው ብለዋል።
በዚህም እንደ ኮሪደር ልማት ዓይነት የልማት ስራዎች የሰመራ ከተማን ገፅታ በመቀየርና ለነዋሪዎች ምቹ መሆንን ለአብነት አንስተዋል።