የነዳጅ አቅርቦት እጥረትን ለመቋቋም የተወሰደው የመፍትሄ አቅጣጫ ተግባራዊነቱ እንደቀጠለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የነዳጅ አቅርቦት እጥረትን ለመቋቋም የተወሰደው የመፍትሄ አቅጣጫ ተግባራዊነቱ እንደቀጠለ ነው
ደሴ ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦ የነዳጅ አቅርቦት እጥረትን ለመቋቋም የተወሰደው የመፍትሄ አቅጣጫ በተቀናጀ መልኩ ተግባራዊነቱ እንደቀጠለ መሆኑን የደሴ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት ምክንያት የተከሰተውን የነዳጅ አቅርቦት ችግር ለመቋቋም በመንግስት በኩል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑ ይታወቃል።
የነዳጅን አጠቃቀምን በቁጠባ ማድረግ፣ የታዳሽ ኃይል አማራጮችን የመጠቀም ልምድ፣ የእግር ጉዞ ባህልን ማጎልበት፣ የሕዝብ ትራንስፖርትን መጠቀም፣ በነዳጅ ግብይት ላይ የሚስተዋሉ ሕገ-ወጥ ተግባራትን መቆጣጠር ትኩረት የተደረገባቸው ጉዳዮች ሆነዋል።
በደሴ ከተማ እና አካባቢው ያለውን የነዳጅ አጠቃቀምና አጠቃላይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አተገባበር በተመለከተ ኢዜአ የደሴ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮናስ እንዳለ ጋር ቆይታ አድርጓል።
ኃላፊውም በማብራሪያቸው የነዳጅ አቅርቦት እጥረትን ለመቋቋም የተወሰደው የመፍትሄ አቅጣጫ በተቀናጀ መልኩ ተግባራዊነቱ እንደቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል።
የእስካሁኑ ሂደት በብዙ መልኩ ሲታይ ውጤታማ እንደነበር አስታውሰው ችግሩ በዘላቂነት እስከሚፈታ ድረስ ለመፍትሄው በጋራ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ግብረ ሃይል በማቋቋም ቅድሚያ ለሚሰጠው በመስጠትና ሌሎች መንግስት ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ተግባራዊ ማድረግ መቻሉን አስታወሰው ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡም ችግሩ አለም አቀፍ መሆኑን በመገንዘብ በእግሩ በመጓዝ፣ ጉዞዎችን በመቀነስ፣ በመተባበርና በመረዳዳት ያሳየው መልካም ተግባር የከፋ ችግር እንዳይፈጠር አስችሏል ብለዋል።
በደሴ ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪ የሆነው ወጣት ሰይድ ይመር፤ የምናገኘውን ነዳጅ በአግባቡ በመጠቀም የህዝብ አገልግሎት እየሰጠን እንገኛለን፤ አጠናክረንም እንቀጥላለን ብሏል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ታደሰ ኪዳነማሪያም፤ የነዳጅ አቅርቦት ችግሩ ፈታኝ ቢሆንም ለቀጣይ ብዙ የሚያስተምረን ነገር አለ ብለዋል።
የነዳጅ አቅርቦት ችግሩን ተቋቁሞ ለማለፍ በመንግስት የተቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አድንቀዋል።
በተለይም የነዳጅ ጥገኝነትን በመቀነስ አማራጭ መንገዶችን ማብዛትና የኤሌክትሪክ ሃይል ልማትን ማስፋት ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።