ቀጥታ፡

በጅግጅጋ ከተማ ለበዓል ገበያ የእርድ እንስሳትና የፍጆታ ምርት በበቂ ሁኔታ ቀርቧል

ጅግጅጋ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦በጅግጅጋ ከተማ ለበዓል  ገበያ በቂ የእርድ እንስሳትና የግብርና ምርቶች  አቅርቦት መኖሩን ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለጹ።

በጅግጅጋ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነጋዴዎችና ሸማቾች ለዘንድሮው የትንሣዔ በዓል በከተማዋ በቂ የእርድ እንስሳትና ሌሎች የፍጆታ ምርቶች አቅርቦትና ግብይት መኖሩን ገልጸዋል።

ወይዘሮ ሲሃም በድሪ በአትክልት ምርቶች ንግድ ላይ የተሠማሩ ሲሆኑ በበዓል ገበያው በቂ ምርት መኖሩን በመግለፅ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ  አለመታየቱን እና በአሁን ወቅት በምርት አቅርቦት በኩል ችግር አለመኖሩን ገልጸዋል።

ከፍየል ነጋዴዎች መካከል ወይዘሮ አሚና ዩሱፍ በገበያው በቂ የእርድ እንስሳት መቅረቡን ተናግረዋል።

በእንቁላል ምርት ሽያጭ ላይ የተሠማሩት አቶ ታረቀኝ ጀምበሩ በበኩላቸው ለበዓሉ በቂ ምርት መኖሩን ጠቅሰዋል።

የጅግጅጋ ከተማ ንግድና ገበያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ  ለይላ መሀመድ በበኩላቸው፤  ለትንሳኤ የበዓል ገበያ የግብርናና የፋብሪካ ምርቶች እጥረት እንዳይፈጠር ከህብረት ስራ ማህበራት ጋር በቅንጅት መሰራቱን አንስተዋል።

የበዓል ምርቶቹን በበቂ ሁኔታ ከማቅረብ ባለፈ ህገ ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር  ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም