በድሬዳዋ መንግስት በነዳጅ አጠቃቀምና ስርጭት ላይ ያስቀመጠው መመሪያ በአግባቡ እየተተገበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በድሬዳዋ መንግስት በነዳጅ አጠቃቀምና ስርጭት ላይ ያስቀመጠው መመሪያ በአግባቡ እየተተገበረ ነው
ድሬዳዋ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦) መንግስት በነዳጅ አጠቃቀምና ስርጭት ላይ ያስቀመጣቸው መመሪያዎችና አቅጣጫዎች በአግባቡ በመተግበር ላይ መሆናቸውን የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሚኖ ጣሃ ተናገሩ።
የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በነዳጅ አቅርቦትና ግብይት ላይ መጠነ ሰፊ ችግሮችና ተፅዕኖዎችን አስከትሏል።
ኢትዮጵያም ሊደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም የሚያስችሉ የተለያዩ የመፍትሄ አቅጣጫዎች እና መመሪያዎችን ዘርግታ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች።
በድሬዳዋ በነዳጅ አቅርቦትና ስርጭት ላይ ሊገጥም የሚችለውን ችግር ለመቋቋም የተቀመጡ የመፍትሄ አቅጣጫዎች በአግባቡ በመተግበር ላይ መሆኑን የአስተዳደሩ ንግድ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሚኖ ጣሃ ለኢዜአ ተናግረዋል።
የአስተዳደሩ የፍትህና ፀጥታ ተቋማትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የተካተቱበት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ መመሪያው በአግባቡ እንዲተገበር በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በከተማው በሚገኙ 30 የነዳጅ ማደያዎች ለሊት ጭምር ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ነዳጅን በተቀመጠው መመሪያ በፍትሃዊነት ተደራሽ እያደረጉ መሆኑንም አንስተዋል።
በየማደያዎቹም ከጅቡቲ ነዳጅ ለሚያጓጉዙት፣ ወደ ውጭ የሚወጡ ምርቶችን ለሚያመርቱት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎችና ሌሎችም ቅድሚያ በመስጠት እንቅስቃሴያቸውን በማሳለጥ ላይ መሆናቸውን በመግለፅ።
የተቀሩትም መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የስርጭቱ ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው ብለዋል።
የመንግስት ተሸከርካሪዎችም ነዳጅን በቁጠባና በጋራ እንዲጠቀሙ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
የብዙሃን ትራንስፖርትና ሀገር አቋራጭ ተሸከርካሪዎች እንዲሁም ትኩረት ለሚሹ አገልግሎት ሰጪ የአስተዳደሩ ተቋማትም ነዳጅ እንዲደርሳቸው እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን መንግስት ያወጣውን መመሪያ ያላከበሩ አራት ማደያዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ከድርጊታቸው እንዲመለሱ መደረጉንም አቶ አሚኖ አውስተዋል።
በአንጻሩ መመሪያዎችን በግንባር ቀደምትነት ተቀብለው በተሳካ መንገድ እየፈፀሙ የሚገኙ 8 ማደያዎች ደግሞ አስተዳደሩ ምስጋናና ዕውቅና እንደሰጣቸው በማስታወስ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው አሽከርካሪዎች በበኩላቸው መንግስት በከፍተኛ ድጎማና ውስብስብ ችግር የሚያቀርበውን ነዳጅ በቁጠባና ከብክነት በፀዳ መንገድ ማሰራጨቱ ወቅታዊ ችግር የሚያሻግር መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ወንድወሰን አበራ እና ሸምሰዲን ኢድሪስ የተባሉ የህዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች በበኩላቸው እንዳሉት፤ መመሪያው ነዳጅን በፍትሃዊነት ለማሰራጨትና ለመቆጠብ የሚያስችል መፍትሄ ነው ብለዋል።