ከለውጡ ወዲህ ለቱሪዝም ተኮር የቅርስ ልማት የተሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያን ቱሪዝም ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከለውጡ ወዲህ ለቱሪዝም ተኮር የቅርስ ልማት የተሰጠው ትኩረት የኢትዮጵያን ቱሪዝም ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ ነው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦መንግሥት ለቱሪዝም ተኮር የቅርስ ጥበቃና ልማት የሰጠው ልዩ ትኩረት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን በማድረግ ለዘርፉ ዕድገት የጎላ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረትና በነደፈው የብዝኃ ዘርፍ ፖሊሲ አማካኝነት፣ ለዘመናት የተዘነጉ በርካታ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ተገቢውን ጥገናና እድሳት አግኝተው ለጎብኚዎች ክፍት ሆነዋል።
የጎንደር አብያተ መንግሥታት፣ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት፣ ጂማ አባ ጅፋር ቤተ መንግሥት፣ ሐረር ጀጎል ግንብ፣ ሶፍ ኡመር ዋሻን ጨምሮ በአዲስ አበባና ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ታድሰው ለጎብኝዎች ክፍት ሆነዋል።
የኢትዮጵያ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ መንግሥት ዘርፉን ለማሳደግ በወሰደው ቁርጠኝነት ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን የማልማት ተግባር በውጤታማነት እየተከናወነ ይገኛል።
በተለይም ለባህልና የከተማ ቱሪዝም ትኩረት በመሰጠቱ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገቡን በማንሳት፥ የኢትዮጵያ የቅርስ ልማት ሥራ የቱሪዝም ዘርፉን ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገረ ነው ብለዋል።
በለውጡ ዓመታት የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ የኢትዮጵያን ክብርና ታሪክ ከቱሪዝም የሚያስተሳስሩ ሙዚየሞችም መገንባታቸውን ገልጸዋል።
የቅርስ ቦታዎችን የማዘመን ስራ የኢትዮጵያን ገጽታ ከመገንባቱ ባለፈ፣ የጎብኝዎችን ቁጥር በመጨመር የቱሪዝም ገቢን ማሳደጉንና ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል።
ቅርሶች በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ የተደረገው ጥረት ለሀገሪቱ ታሪካዊ እሴቶች ተገቢውን ክብር አስገኝቷል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 19 ቅርሶችን በዩኔስኮ በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚ ሥፍራ መያዟን ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅትም ቋሚና የማይዳሰሱ ቅርሶችን የማስመዝገብ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን አስታውቀዋል።
ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከልም የአገው ፈረስ ባህል፣ የሀላባ የዘመን መለወጫ 'ሴራ' እንዲሁም ዋዛ የሙዚቃ መሳሪያ ጨዋታ (ዙምባራ) በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ ቀርበዋል ነው ያሉት።
የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውና አስቸኳይ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸውን ቅርሶች ለመጀመሪያ ጊዜ ለማስመዝገብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በጣና ሐይቅ የሚገኙ ደሴቶችንና የአልነጃሺ ታሪካዊ መንደርን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ የተጀመሩ ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኙ ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በዩኔስኮ የሚመዘገቡ ቅርሶች ትኩረት ያደረገው የባህል ቅርሶች ላይ መሆኑን አንስተው በአሁኑ ወቅትም የተፈጥሮ ቅርሶችን ለማስመዝገብ እየተሰራ ነው ብለዋል።