በሊጉ ፋሲል ከነማ ከሃዋሳ ከተማ ነገሌ አርሲ ከኢትዮጵያ መድን ይጫወታሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሊጉ ፋሲል ከነማ ከሃዋሳ ከተማ ነገሌ አርሲ ከኢትዮጵያ መድን ይጫወታሉ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 1/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት ሳምንት ዛሬ አራት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማ ከሃዋሳ ከተማ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ፋሲል ከነማ በሊጉ ባደረጋቸው 25 ጨዋታዎች ስምንቱን ሲያሸንፍ በአምስቱ ተሸንፏል። በቀሪ 12 ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 17 ግቦችን ሲያስቆጥር 15 ጎሎችን አስተናግዷል።
ቡድኑ በ36 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ተጋጣሚው ሃዋሳ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው 25 ጨዋታዎች መካከል 11ዱን ሲያሸንፍ ስድስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። ስምንት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 30 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 20 ግቦችን አስተናግዷል።
ሃዋሳ ከተማ በ41 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።
ባለፉት ስምንት የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው ፋሲል ከነማ ማሸነፍ ከድል ጋር ያስታርቀዋል።
ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታ ያላሸነፈው ሃዋሳ ከተማ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት ሶስት ነጥብ ማግኘት ይጠበቅበታል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ነገሌ አርሲ ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ በሊጉ እስከ አሁን 25 ጨዋታዎችን አከናውኖ 11 ጊዜ ሲያሸንፍ ስድስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ስምንት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። 24 ግቦችን ሲያስቆጥር 17 ጎሎች ገብተውበታል።
ነገሌ አርሲ በ41 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን ይዟል።
በውድድር ዓመቱ ካደረጋቸው 25 ጨዋታዎች መካከል ስድስቱን ያሸነፈው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ ዘጠኝ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ 10 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። 19 ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ በተመሳሳይ 19 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
መድን በ28 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ነገሌ አርሲ ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን የሚያስገኝ ሲሆን በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኛል።
በ25ኛ ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና 1 ለ 0 የተሸነፈው የወቅቱ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ መድን ሶስት ነጥብ ከወራጅ ቀጠና እንዲወጣ ያደርገዋል።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አርባምንጭ ከተማ በ22 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል። ሀዲያ ሆሳዕና በ29 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አርባምንጭ ከተማ ካሸነፈ ተከታታይ ድሉን ያስመዘግባል። ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ፉክክርም ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከወላይታ ድቻ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ወልዋሎ በ29 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ወላይታ ድቻ በ28 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል።
በ25ኛ ሳምንት ከሃዋሳ ከተማ ጋር ሁለት አቻ የተለያየው ወልዋሎ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።
ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አቻ የወጣው ወላይታ ድቻ ማሸነፍ ካለበት የመውረድ ስጋት መጠነኛ እፎይታ እንዲያገኝ ያስችለዋል።