በአማራ ክልል በከተማ ክላስተር ዘርፍ አመርቂ ስኬቶች ማስመዝገብ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል በከተማ ክላስተር ዘርፍ አመርቂ ስኬቶች ማስመዝገብ ተችሏል
ባህር ዳር፤ መጋቢት 30/2018(ኢዜአ) ፦በአማራ ክልል በከተማ ክላስተር ዘርፍ አመርቂ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሃመድ (ዶ/ር) ገለፁ።
በክላስተሩ ተቋማት በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራትን የሚገመግም የውይይት መድረክ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ አህመዲን መሃመድ (ዶ/ር) በመድረኩ እንደገለጹት፤ አመራሩ ከባለሙያው ጋር ባደረገው ቅንጅት በከተማ ክላስተር ዘርፍ ስኬት ሊመዘገብ ችሏል።
ለዚህም በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ የኢንዱስትሪ መንደሮችን በማስፋፋት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና ገጠርን ከከተማ በማስተሳሰር የተገኘ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።
ሥራውም በተለይ የኮሪደር ልማት የከተሞችን ውበትን የገለጠ፣ የህብረተሰቡን የሥራ ባህል የቀየረ እና ከተሞችን ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ተመራጭ ያደረገ ነው ብለዋል።
እንደ አህመዲን (ዶ/ር) ገለጻ ለውጭ ባለሃብቶች ብቻ ተፈቅዶ የነበረው በኢንዱስትሪ መንደሮች ገብቶ የማልማት ሥራ ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶችም መፈቀዱ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ዘርፉ እንዲነቃቃ አድርጓል።
በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በኩልም 5 ሚሊዮን ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ማውጣታቸውን ጠቅሰው በኢትዮ-ኮደርስ በርካታ ወጣቶችና ሠራተኞች የስልጠናው ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።
በቀሪ ወራትም በከተማ ክላስተር ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠልና ክፍተቶችን በማረም የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
የክልሉ ከተሞችና መሰረተ ልማት ቢሮ አማካሪ አቶ ሽቤ ክንዴ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ በ32 ከተሞች የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች፣ የአረንጓዴ ልማትና የመዝናኛ ስፍራዎችን ያሟላ የኮሪደር ልማት ግንባታ እየተከናወነ ነው።
በቀሪው ጊዜም በዕቅድ የተያዘውን በጥራት ገንብቶ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ ህብረተሰቡም በልማቱ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የአማራ ከልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ የቻለ ይግዛው፤ የክላስተር ቢሮዎች አሰራራቸውን እንዲያዘምኑና የሚሰጡት አገልግሎት ቀልጣፋና ተደራሽ እንዲሆን ለማድረግ ቢሮው በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።
በኢንቨስትመንት፣ በንግድና ገበያ ልማት፣ በቱሪዝምና ሌሎች ተቋማት የዲጂታል ቴክኖሎጂ አሰራርን በማስፈን ለህብረተሰቡ የሚሰጡ አገልግሎቶች ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ከብልሹ አሰራር የጸዱ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የዲጂታል ትግበራውም የክልሉን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መስተጋብር ከማፋጠን ባሻገር ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድግ አበረታች ውጤት እያስገኘ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ በክላስተሩ ሥር የሚገኙ ተቋማት ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።