ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ጃፓን በፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ መከሩ

አዲስ አበባ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ጃፓን በፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች ትብብርና አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ መምከራቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መረጃ በጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ኦው ሳዳማና በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ የተመራ የልዑካን ቡድን ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አሰፋ አብዩ እና ከተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች በተመለከተ የሚደረጉ ትብብሮችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ምክክር ተደርጓል።


 

ኢትዮጵያና ጃፓን ከዚህ ቀደም በደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ የሚሠሯቸውን ተግባራት በማጠናከር በቀጣናው የሚንቀሳቀሱ ሽብርተኛ ቡድኖችንና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል መክረዋል።

በሳይበርና በአቪዬሽን ደኅንነት ዙሪያ የሚደረጉትን ትብብሮችና የመረጃ ልውውጦች ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮችም ላይም ተወያይተዋል።     

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር አሰፋ አቢዩ፤ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የተከናወኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንዲሁም የፀጥታ ዘርፍ ሪፎርሞችን በተመለከተ ለጃፓን ልዑክ አባላት ገለጻ አድርገዋል። 

በዚህ ወቅት የሪፎርም ሥራዎቹን ፋይዳም አብራርተዋል፡፡


 

ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል  ዶክተር አሰፋ አቢዩ፤  ኢትዮጵያ በሰላማዊ አማራጭ መንገዶች የባሕር በር ተደራሽነትን ለማረጋገጥ  የጀመረቻቸውን እንቅስቃሴዎች ለልዑካን ቡድኑ አስረድተዋል።

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ኦው ሳዳማና በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት አኳያ የሁለቱን ሀገራት ትብብርና አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ይሰራል፡፡

ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር በመረጃና በልምድ ልውውጥ እንዲሁም በአቅም ግንባታ መስኮች የተጀመሩ የአጋርነት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባሕር በር ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የጀመረቻቸውን ጥረቶች ጃፓን እንድምትደግፍ ገልፀዋል።


 

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ያደነቁት የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ፤ በአጭር ዓመታት ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ያመጣ ሪፎርምና ትላልቅ የከተማ ልማት ሥራዎችን መሥራቷ ለሌሎች በአብነት የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም