በገንዳውኃ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ከ950 ሊትር በላይ ነዳጅ ተያዘ - ኢዜአ አማርኛ
በገንዳውኃ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ የተከማቸ ከ950 ሊትር በላይ ነዳጅ ተያዘ
ገንዳውኃ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳውኃ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የነበረ ከ950 ሊትር በላይ ነዳጅ መያዙን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንስፔክተር ሀይሌ ብርሃኑ 900 ሊትር ናፍጣ እና 56 ሊትር ቤንዚን በግለሰብ ቤት ከተደበቀበት ለመያዝ መቻሉን ገልጸዋል።
በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ የነበረው ነዳጅ ሊያዝ የቻለው የጸጥታ አካላት ባደረጉት ድንገተኛ ፍተሻና ጥብቅ ክትትል መሆኑንም ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ነዳጁ በህገወጥ መንገድ ተከማችቶ የተገኘው በከተማው ቀበሌ 03 ልዩ ቦታው ቀጠና 08 በተባለ አካባቢ ነው።
በቀጣይም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና የሚፈጥሩ መሰል ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የቁጥጥር ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ህብረተሰቡ ህገ ወጥ ተግባር ተፈጽሞ ሲያይ ለጸጥታ አካላት ፈጥኖ ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ትብብር በቀጣይም አጠናክሮ እንዲቀጥል ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።