ቀጥታ፡

የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ በባህር ዳር ከተማ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ማዕድ የማጋራት ተግባር ተከናወነ 

ባህር ዳር ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦መጪውን የፋሲካ በዓል ምክንያት በማድረግ በባህር ዳር ከተማ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርሀግብር ተከናወነ።

የከተማ አስተዳደሩ ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሰብለ ዘውዱ በማዕድ ማጋራት መርሀግብሩ ላይ እንደገለጹት፣ በዓልን በመደጋገፍ በአብሮነት የማሳለፍ እሴት ተጠናክሮ ቀጥሏል።


 

በተለይም ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የተለያዩ አካላትን በማስተባበር አቅመ ደካማ ወገኖች በዓልን ተደስተው እንዲያሳልፉ የተጀመረው የድጋፍ ሥራ ውጤት እየታየበት መሆኑን ተናግረዋል። 

በዛሬው እለትም ለ400 አቅመ ደካሞች የበዓል መዋያ ድጋፍ መደረጉን ገልጸው፣ በዚህም ለእያንዳንዳቸው የዳቦ ዱቄት፣ የዘይት እና የዶሮ ድጋፍ  ተደርጓል ብለዋል።

መምሪያው ባለድርሻ እና አጋር አካላትን በማስተባበር ከሚያደርገው ከዕለታዊ ድጋፍ በተጨማሪ ለዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ  ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ወይዘሮ ሰብለ አስረድተዋል።

ከድጋፉ ተጠቃሚዎች መካከል ወይዘሮ እናት በሽር በሰጡት አስተያየት የተደረገላቸው ድጋፍ በዓሉን ያለሀሳብ ከቤተሰባቸው ጋር ተደስተው ለማሳለፍ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።


 

ድጋፍ ላደረጉላቸው አካላት ምስጋናቸውን ያቀረቡት ወይዘሮዋ፣ ድጋፉ ተጠናክሮ ሌሎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

አቶ አስማረ አያሌው የተባሉ ሌላው የማዕድ ማጋራቱ ተጠቃሚ በበኩላቸው በአቅም ማነስ ለበዓል እየተጨነቁ ባለበት ወቅት  የድጋፉ ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ነው የገለጹት።

በዛሬው እለት የተደረገላቸው የበዓል መዋያ ድጋፍ በዓሉን ከቤተሰባቸው ጋር በአብሮነትና በደስታ ለማሳለፍ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም