ኢትዮጵያና ጃፓን በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ጃፓን በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2018(ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያና ጃፓን በጋራ ፍላጎቶቻቸውና በጸጥታ ጉዳይ ላይ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ኦዌ ሳዳማሳ የተመራውን የልዑካን ቡድን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
በቆይታቸውም የሁለቱን አገራት ብሄራዊ ጥቅሞች፣ የጋራ ፍላጎትና እሴቶችን ባከበሩ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በአህጉር ደረጃ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የምታከናውናቸውን ተግባራት ልዩ አማካሪው ኦዌ ሳዳማሳ አድንቀዋል።
በተለይም በሰላም ማስከበር ረገድ ያላትን ሰፊ ተሞክሮ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ጃፓን በዚህ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ያላትን ከፍተኛ ፍላጎት አረጋግጠዋል።
ጃፓን የኢትዮጵያን የሰላም ማስከበር ማዕከል አቅም ለመገንባት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን የጠቆሙት አማካሪው፤ በስልጠና እና በልምድ ልውውጥ የመከላከያ ሰራዊቱን የሰው ኃይል የሙያ ብቃት ለማሳደግ ያላቸውን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል።
ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው፣ ጃፓን ለትብብር ያሳየችውን ተነሳሽነት በማድነቅ፤ ኢትዮጵያ በእውነተኛ ወዳጅነትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ወታደራዊ አጋርነትን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል።
ይህ ትብብርም በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የቆየ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ያላቸውን እምነት መግለጻቸውን ኢዜአ ከመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያሳያል።