ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ለአፍሪካ ምሳሌ ናቸው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ በኮሪደርና በወንዝ ዳርቻ ልማት የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከልና ምላሽ ለአፍሪካውያን ምሳሌ የሆኑ ተግባራትን እያከናወነች እንደምትገኝ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት 16ኛው የአፍሪካ አደጋ ሥጋት አቅም አህጉራዊ ጉባኤ "ለሉዓላዊነት መተባበር" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እየተካሄደ ነው።


 

39 የአፍሪካ አደጋ ሥጋት አቅም አባል ሀገራትና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን እየተሳተፉበት የሚገኘው ይህ ጉባኤ፤ በአፍሪካውያን መካከል ትብብርና አጋርነትን በመፍጠር አህጉራዊ የአደጋ ሥጋትን የመከላከልና የፋይናንስ አቅምን ማጠናከርን ያለመ ነው።

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ አፍሪካውያን የምግብ ሉዓላዊነትን  በራሳቸው አቅም ለማረጋገጥ ለጋራ ግብ የሚተባበሩበት ወሳኝ ወቅት ላይ ናቸው፡፡

የአፍሪካ የአደጋ ሥጋት አቅም አህጉራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን በራስ አቅም ለማሳካት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸው፤ የተቀናጀ የአደጋ ሥጋት ምላሽ መስጠት የሚያስችል አህጉራዊ የፋይናንስ አቅም መገንባት ይገባል ብለዋል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ግቦችን በማሳካት የምንመኛትን አፍሪካ ለመገንባት የሀገራት ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ስርዓት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ቀዳሚ አጀንዳ መደረጉን ገልጸው፤ ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር የተሟላ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል አቅም ተገንብቷል ብለዋል፡፡


 

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ መስኖ፣ የሌማት ትሩፋት፣ የታዳሽ ኃይል እና ሌሎችም ኢንሼቲቮች የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመከላከል እንዲሁም የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን በመመከት፣ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥና የአደጋ ምላሽ በመስጠት ለአፍሪካና ለዓለም ምሳሌ እየሆነች ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማትና ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ያሳየችው ስኬት ጉባኤውን ለማስተናገድ ተመራጭ እንዳደረጋትም ኮሚሽነሩ አንስተዋል።

የአፍሪካ አደጋ ስጋት አቅም ጉባኤ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም በማሟላትና የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ያስመዘገበቻቸውን ተሞክሮዎች የምታጋራበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ሥርዓት ለመገንባት የተገበረቻቸው ኢኒሼቲቮች የምግብ ሉዓላዊነትን እና የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ማሳካት እንደሚያስችሉ ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ የሚሰሩ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች የአየር ንብረት ለውጥን መከላከልና የአደጋ ምላሽ በመስጠት ለአፍሪካውያን ምሳሌ የሆኑ የተግባር ማሳያዎች ናቸው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም