ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ከሞሮኮ፣ ቱኒዚያ እና ግብጽ ጋር ተደለደለች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦ በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 16ኛው ከ17 ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል ዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ዛሬ በግብጽ ካይሮ ተካሄዷል።

በዚሁ መሰረት ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ሞሮኮ፣ቱኒዚያ እና ግብጽ ጋር ተደልድላለች።

በአሜሪካው አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለውድድሩ በአዲስ አበባ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።

በዕጣው መሰረት በምድብ ሁለት ኮትዲቯር፣ ካሜሮን፣ ዩጋንዳ እና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተደልድለዋል።

ማሊ፣ አንጎላ፣ ታንዛንያ እና ሞዛምቢክ በምድብ ሶስት የሚገኙ ሀገራት ናቸው።

ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያ እና ጋና የሚገኙበት ምድብ አራት ጠንካራው ምድብ ነው።

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሕዳር ወር 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሶስተኛ መውጣቱን ተከትሎ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ የሚታወስ ነው። 

16ኛው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ከሚያዚያ 17 እስከ ግንቦት 7 ቀን 2018 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። በውድድሩ ላይ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።

በአፍሪካ ዋንጫው ከሚሳተፉ 16 ሀገራት መካከል የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ 10 ሀገራት በጥቅምት እና ህዳር ወር 2019 ዓ.ም በኳታር ለሚካሄደው 20ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም