የጉምሩክ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የጉምሩክ አገልግሎት በሚያቀላጥፍ መልኩ እየተዘጋጀ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የጉምሩክ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የጉምሩክ አገልግሎት በሚያቀላጥፍ መልኩ እየተዘጋጀ ነው
አዲስ አበባ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦የጉምሩክ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የጉምሩክ አገልግሎት በሚያቀላጥፍ መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
ቋሚ ኮሚቴው በጉምሩክ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ የአስረጂ መድረክ አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የፕላን በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ፤ በረቂቅ አዋጁ ሥርዓት ክፍተትን የሚያርሙ ድንጋጌዎች እንደተካተቱ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን አህጉራዊና ዓለም አቀፍ የንግድ ተወዳዳሪነትን የሚያሳልጥ ዓለም አቀፍና አዳዲስ የጉምሩክ አገልግሎት ማቀላጠፊያ ድንጋጌዎች መካተታቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የአዋጁ ማሻሻያ የኮሚሽኑን ተግባርና ኃላፊነት በተቀላጠፈ የአሰራር ሥርዓት በመምራት ውስብስብ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን መግታት በሚያስችል መልኩ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል።
የምክር ቤቱ አባላትና የሕግ ሙያተኞችም፤ በረቂቅ አዋጅ ላይ ምላሽና ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮችን በማስመልከት ለሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች አስተያየትና ጥያቄ አቅርበዋል።
በረቀቂ አዋጁ ላይ የገቢ ምርቶችን የቆይታ ጊዜ በማስመልከት ከዚህ ቀደም ከነበረው አንፃር ሲታይ ከፍ እንዲል መደረጉን በማስመልከት ምላሽና ማብራሪያ ጠይቀዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በምላሽና ማብራሪያቸው፤ የጉምሩክ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ከዚህ ቀደም የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን ለማረም ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
በዚህም በረቂቅ አዋጁ ውስብስብ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን መከላከል የሚያስችሉ ወሳኝ ድንጋጌዎችን በማካተት እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አዘዘው ጫኔ በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያን የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት የሚያቀላጥፍ አስቻይ የጉምሩክ አገልግሎት አሰጣጥ ተቋማዊ የሪፎርም አካል መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በዕቃዎች የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት የሚጠናቀቅበት ጊዜ፣ የዋጋ አወሳሰን፣ በይግባኝ አቀራረብ፣ በጉምሩክ ጥሰት የሚወረሱ ንብረቶች አስተዳደር፣ የዋስትና አያያዝ ላይ የተደረጉ ጉልህ ማሻሻያዎች ላይም ማብራርያ ሰጥተዋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር የታክስ ጉዳዮች አማካሪ ዋሲሁን አባተ፤ በረቀቂ አዋጁ ላይ የጉምሩክ ሥነ-ስርዓትን ያሟላ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ወሳኝ ድንጋጌዎች መካተታቸውን አስረድተዋል።
በዚህም በረቂቅ አዋጁ ላይ የጉምሩክ አገልግሎቶችን የሚያቀላጥፉ አመቺና አዳዲስ ዓለም አቀፍ የአሰራር ሥርዓት መርሆችና ድንጋጌዎች እንደተካተቱ አስገንዝበዋል።