ቀጥታ፡

በጉጂ ዞን በበልግ አዝመራ ከ260 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል

አዶላ ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በበልግ አዝመራ ከ260 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ መንግስቱ ሂርባዬ በዞኑ በበልግ አዝመራ 294 ሺህ 389 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን  ዕቅድ ተይዟል ብለዋል።

እስካሁን በተካሄደው ስራም  260 ሺህ 780 ሄክታር መሬት በአራት ዋና ዋና ሰብሎች በዘር መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡


 

የተጠቀሰው ሄክታር መሬትም በበቆሎ፣ በስንዴ፣ በጤፍ፣ በቦሎቄና በሌሎች ሰብል ዘር መሸፈኑን ገልጸው  የግብርና ስራውን ለማሳካትም  የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦቱም በወቅቱ ለአርሶ አደሩ መድረሱን ጠቁመዋል።

በዘር ከተሸፈነው መሬትም እስካሁን 239 ሺህ 230 ሄክታር በመስመር፣ 175 ሺህ 209 ሄክታሩ ደግሞ በኩታ ገጠም የእርሻ ስነ-ዘዴ መልማቱን አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ ቆላማ አካባቢ የዝናቡ ስርጭት የሚቆየው ለተወሰነ ጊዜ በመሆኑ የዘር ስራውን ለማፋጠን በርካታ ትራክተሮች መሰማራታቸውን  ጠቅሰዋል፡፡

በበልግ   አዝመራ ልማቱ  ከ95 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡

ምርታማነቱን ለማሳደግም ከ95 ሺህ 403 ኩንታል በላይ ማዳበሪያና 42 ሺህ 262 ኩንታል የምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ መከፋፈሉንም አብራርተዋል፡፡

በዞኑ በበልግ አዝመራ ከሚለማው መሬትም  ከ7 ሚሊዮን 175 ሺህ ኩንታል በላይ  ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል ብለዋል፡፡


 

በዞኑ አዶላ ወረዳ የሞኤ ቦኮ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሹና ጎበና ለበልግ አዝመራ ያዘጋጁትን መሬት በዘር በመሸፈን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ምርታማነታቸውንም ለማሳደግ  የአፈር ማዳበሪያ ምርጥ  ዘር መጠቀማቸውን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ያለው ደጋ፣ ወይና ደጋና ቆላማ የአየር ጸባይ ለሰብል ልማትና ለእንስሳት እርባታ አመቺ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም