ቀጥታ፡

ወጣቶች በምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ መጎልበት ሚናቸውን ማጠናከር አለባቸው  

አዲስ አበባ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦ወጣቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ መጎልበት ሚናቸውን ማጠናከር እንዳለባችው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ገለጹ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር  "በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የወጣቶች ድምፅና ተሳትፎ ለሠላምና ለዴሞክራሲ“ በሚል መሪ ሀሳብ የወጣቶች ተሳትፎን ለማጎልበት ያለመ የንቅናቄ መርሃ ግብር አካሂዷል። 


 

በመርሃ ግብሩ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ እንደገለጹት፤ ወጣቶች የዲሞክራሲያዊ ስርዓቱ ዋነኛ ምሰሶ በመሆናቸው በምርጫ ሂደቱ ንቁ ተሳታፊ ሊሆኑ ይገባል።

በዚህም የሀገሪቱን የልማትና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ጉዞን ለማፋጠን እንደሚቻል ጠቁመው፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በወጣቶች ሙሉ ተሳትፎ የታጀበ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንስራ ብለዋል።

በዚህም በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ለመጻኢ እድል ወሳኝ መደላድልን ማመቻቸት አለባችሁ ብለዋል።

በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው የወጣቶች ተሳትፎ ተስፋ ሰጪና ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ጠንካራ መሠረት የጣለ እንደነበር አንስተዋል። 

በምርጫው ከ150 ሺህ በላይ ወጣቶች በምርጫ አስፈጻሚነትና በታዛቢነት መሰማራታቸውን ገልጸው፤  በዚህም ወጣቶች ለዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ የጀርባ አጥንት መሆን እንደሚችሉ በተግባር አሳይተዋል ብለዋል።


 

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይህንን ተሳትፎ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚገባ ተናግረዋል። 

ወጣቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያቀርቧቸው ማኒፌስቶዎች ውስጥ የወጣቶች አጀንዳ በትክክል መካተቱን መመርመርና በጥብቅ መከታተል ያስፈልጋል ብለዋል።

የወጣቶች በምርጫ መሳተፍ ለስራ እድል ፈጠራ፣ የኢንተርፕራይዞች መስፋፋት፣ የብድር አቅርቦትና የፈጠራ ስራዎች ድጋፍ ምላሽ የሚሰጥ መንግስትና ፖሊሲ ለመምረጥ ያስችላል ሲሉም ተናግረዋል።

በንቅናቄው መርሃ ግብር የተሳተፉ ወጣቶችም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ ሀላፊነታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረው፤ሌሎች ወጣቶችም  በንቃት ሊሳተፉ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት አባል የሆኑት ወጣት በቃሉ መሰረት እና የምስራች ቶማስ ምርጫ በሀገር ጉዳይ ላይ መወሰን በመሆኑ ወጣቶች ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ እስከ ድህረ ምርጫው ባለው ሂደት በንቃት ሊሳተፉ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም