ሰባተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
ሰባተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦ ሰባተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ሰባተኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፍረንስን በሚመለከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ኮንፍረንሱ ከሚያዚያ 7 እስከ 8 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡
በኮንፍረንሱ ላይ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማፅናት በሚያስችሉና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት የፓናል ውይይት እና ህዝባዊ ውይይት እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ከኮንፍረንሱ በተጨማሪ በክልሉ ያሉ የልማት ስራዎች ጉብኝት፣ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብርና ሌሎች የተለያዩ ሁነቶች እንደሚከናወኑ አብራርተዋል።
ለሁለት ቀናት በሚኖረው ኮንፍረንስ ላይ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚሳተፉም አክለዋል።
ጉባኤው ከዚህ ቀደም በተለያዩ ክልሎች ባካሄዳቸው ስድስት የሰላም ኮንፍረንሶች ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መረጋገጥ አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።
የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ለዜጎች የሰላም ጥሪን በማስተላለፍና በማስተማር ለሰላም ዘብ የሆነ ትውልድን ለመፍጠር ትልቅ ሚና መጫወት ችለዋል ብለዋል።
ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮችም ለስሙነ ህማማት እና ለስቅለት በአል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።