ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ የትንሳኤ በዓልን ሲያከብር  የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል

ጎንደር ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡ የትንሳኤ በዓልን ሲያከብር  የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍና የአብሮነት እሴቱን በማስቀጠል ሊሆን እንደሚገባ ተመላከተ።

በዓላት የህብረተሰቡ የመረዳዳት ባህል የሚታይባቸውና በመደጋገፉ ውስጥ የነበሩ የአብሮነት እሴቶች የሚገለጹባቸው ናቸው።

ይህንንም ከግምት ባስገባ መልኩ በጎንደር ከተማ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር ተካሄዷል።   


 

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ፣ በማዕድ ማጋራት ስነ ስርዓቱ ላይ በመገኘት እንደገለጹት በዓላት ሲመጡ የተቸገሩና አቅመ ደካማ ወገኖችን ማሰብ የዜግነት ግዴታ ነው።


 

የትንሳኤ በዓልን ምእመኑ ሲያከብርም ያለው ለሌለው በማካፈልና የአብሮነት እሴቱን በሚያጠናክር መልኩ በጋራ በዓሉን በማሳለፍ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ገንዘብ መምሪያ የፕሮጀክት ክትትልና የበይነ መንግስታት አስተባባሪ አቶ አበበ ካሴ በበኩላቸው፤ ከማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለ200 አቅመ ደካማ ወገኖች የማእድ ማጋራት መርሃ ግብር ተከናውኗል ብለዋል።


 

በዚህም በከተማው ከሚንቀሳቀሱ 29 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተገኘ 600 ሺህ ብር ለበዓል መዋያ የምግብ ቁሳቁሶችን ጨምሮ ለእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ሺህ ብር መስጠት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ 


 

ከድጋፉ ተጠቃሚዎች መካከል እማሆይ እንይሽ ሽፈራው ለተደረላቸው ድጋፍ አመስግነው በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የአብሮነት እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡


 

ሌላዋ የድጋፉ ተጠቃሚ ወይዘሮ ፍርዴ አስቻለው በበኩላቸው የተደረገልኝ ድጋፍ በዓሉን ከልጆቼ ጋር በደስታ እንዳሳልፍ እድል የፈጠረልኝ በመሆኑ ምስጋናዬ ወደር የለውም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም