ቀጥታ፡

በአፍሪካ የአደጋ ሥጋትን በራስ አቅም ለመመከት ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት መገንባት ይገባል

አዲስ አበባ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦በአፍሪካ የአደጋ ሥጋትን በራስ አቅም ለመመከት የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ሥርዓት መገንባት እንደሚገባ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም(ዶ/ር) ገለጹ።

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት 16ኛው የአፍሪካ አደጋ ሥጋት አቅም አህጉራዊ ጉባኤ "ለሉዓላዊነት መተባበር" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን እየተካሄደ ነው።


 

39 የአፍሪካ አደጋ ሥጋት አቅም አባል ሀገራትና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን እየተሳተፉበት የሚገኘው ይህ ጉባኤ፤ በአፍሪካውያን መካከል ትብብርና አጋርነትን በመፍጠር አህጉራዊ የአደጋ ሥጋትን የመከላከልና የፋይናንስ አቅምን ማጠናከርን ያለመ ነው።

የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)፤ አፍሪካውያን የምግብ ሉዓላዊነትን በራሳቸው አቅም ለማረጋገጥ ለጋራ ግብ የሚተባበሩበት ወሳኝ ወቅት ላይ ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአደጋ ሥጋት አቅም አህጉራዊ የምግብ ሉዓላዊነትን በራስ አቅም ለማሳካት የሚያሳየውን ቁርጠኝነት እንደምትደግፍ ገልጸዋል።

በአፍሪካ አደጋዎችን ለመከላከልና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የጋራ ፍላጎት መኖሩን ገልጸው፤ የተቀናጀ የአደጋ ሥጋት ምላሽ መስጠት የሚያስችል አህጉራዊ የፋይናንስ አቅም መገንባት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ የሀገራት ጠንካራ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና ቀጣይነት ያለው የፋይናንስ ስርዓት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 ግቦችን በማሳካት የምንመኛትን አፍሪካ ለመገንባት ጠንካራ የአፍሪካ አደጋ ሥጋት አቅም መፍጠርና በአባል ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት በመፍጠር የተሟላ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል አቅም እየገነባች መሆኑን አንስተዋል።

በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በታዳሽ ኃይል እና በሌሎችም ኢንሼቲቮች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማትና ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባት ያሳየችው ስኬት ጉባኤውን ለማስተናገድ ተመራጭ አድርጓታል።

በጉባኤው ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማሟላትና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያከናወነቻቸውን ስኬታማ ተሞክሮዎች ታካፍላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም