ቀጥታ፡

ተቋማቱ በጋሞ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ

አርባ ምንጭ፤ መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ) ፡-የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በጋሞ ዞን የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች በድምሩ የ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረጉ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ክልል ጋሞ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፡፡

በዛሬው እለት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የ5 ሚሊየን ብር እንዲሁም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በበኩሉ የ5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

በድጋፍ ርክክቡ ላይ የተገኙት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ይገዙ፤ በኢትዮጵያ በደስታም ሆነ በአስቸጋሪ ጊዜ እርስ በርስ የመተባበርና የመተሳሰብ የዳበረ እሴት መኖሩን ገልጸዋል።

በዚህም መሰረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተጎጅዎች ጎን መሆኑን ለማሳየት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት እገዛችን ይቀጥላል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) ኮሚሽኑ አራት የተለያዩ የግል ድርጅቶችን በማስተባበር የ5 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ድጋፍና እገዛችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በተመሳሳይ በዛሬው እለት የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት 700 ሺህ ብር እንዲሁም 300 ሺህ ብር የሚያወጣ የቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።

የህብረቱ ፕሬዝዳንት ፓስተር ደረጀ ታፈሰ፤ በተከሰተው አደጋና ባደረሰው ጉዳት ማዘናቸውን ገልጸው ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።

የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ሐኪሜ አየለ፤ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ለተጎጂዎች እያደረጉት ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።


 

በእስካሁኑ ሂደትም  ለተፈናቃዮች ሰብአዊ ድጋፍ ከማድረግ ጎን ለጎን መልሶ ለማቋቋም በግብረ-ሃይል የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም