የክልሉን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ባህር ዳር፤መጋቢት 30/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በተሰራው የተቀናጀ የህግ ማስከበር ስራ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ሚሊሻ ኮሚሽን አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፥ የክልሉን ሰላም ለማዝለቅ የተቀናጀ የፀጥታ ማስከበር ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ለዚህም የክልሉ የሚሊሻና ሰላም አስከባሪ ሃይሎች ከሌሎች የፀጥታ አባላት ጋር በመተባበር የፀጥታ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
ባለፉት ጊዜያት በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና መፍጠሩን አንስተው፤መንግስት ችግሩን በመነጋገር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሰፊ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም ታጥቀው ጫካ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የፅንፈኛ ቡድኑ አባላት መንግስት ያቀረበውን የሰላም አማራጭን በመቀበል ወደ ሰላማዊ ኑሮ እየመጡ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
የክልሉ ህዝብ ሰላምና ልማት አጥብቆ ይፈልጋል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ የሰላምን አማራጭ ባልተከተሉ ቡድኖች ላይ የፀጥታ ሃይሉ ህግና ስርዓት የማስከበር ስራውን ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አክለዋል።
የክልሉ የሚሊሻና ሰላም አስከባሪ ሃይሉ መጭው ጠቅላላ ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ስጋት መከናወን እንዲችል ሰፊ ስራ እየተሰራ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
የትንሳኤ በዓልም በሰላም እንዲከበር የተቀናጀ ስምሪት ተሰጥቶ እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመዋል።
በበዓል አከባበሩ ወቅት ህብረተሰቡ ማንኛውንም አጠራጣሪ ሁኔታ ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኝ የፀጥታ ሃይል ጥቆማ በመስጠት የሰላሙ ባለቤት መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።