የሰው ተኮር ስራዎቻችን ማንንም የማይዘነጉና አካታች ናቸው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
የሰው ተኮር ስራዎቻችን ማንንም የማይዘነጉና አካታች ናቸው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦መንግስት እያከናወናቸው ያሉ የሰው ተኮር ስራዎቻችን ማንንም የማይዘነጉና አካታች ናቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች መጪውን የትንሳዔ በዓል ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ ለማህበራዊ ችግር ለተጋለጡ፣ለአካል ጉዳተኞች፣ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው የአገር ባለውለታ አረጋውያንና በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የመንግስት ሰራተኞች በአጠቃላይ ከ233 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መደረጉን አመልክተዋል።
ይህ ተግባር በከተማዋ የማዕከል መስሪያ ቤቶች፣ በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች በስፋት እየተከናወነ ያለ በጎ ተግባር ነው ብለዋል።
ከንቲባዋ አክለውም፥ በሁሉም በዓላት የሚደረገው የማዕድ ማጋራት መርሃ ግብር፣ ድጋፍ የሚሹ የከተማዋን ነዋሪዎች ምን ጎደለ? ብሎ በመመልከትና በመጠየቅ ክፍተታቸውን ለመሙላት የሚከናወንና ለነዋሪዎች ያለውን ክብር የሚገልጽ ሰው ተኮር ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።
ከማዕድ ማጋራቱ ባለፈም አሁን ላይ በመካከለኛው ምስራቅ ባለው ግጭትና በነዳጅ እጥረት ሳቢያ ሊከሰት የሚችለውን ጊዜያዊ የኑሮ ጫና ለማቃለልና የገበያ ጉድለትን ለመሙላት መንግስት ከፍተኛ በጀት መድቦ መሰረታዊ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በዚህም የምርት እጥረት እንዳያጋጥም በተሰራው ስራ በከተማዋ የተረጋጋ የገበያ ሁኔታ እንዲሰፍን መደረጉንም ነው የገለጹት።
እነዚህ ወቅታዊ ችግሮችን ለመሻገር የሚከናወኑ ተግባራት በሙሉ ከለውጡ ወዲህ የተጀመሩ የሰው ተኮር ስራዎች አካል መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፤ አዲስ አበባ ለሀብታሙም ለድሃውም እኩል የተመቸች እንድትሆንና ስራዎቻቸው ማንንም ያልዘነጉ አካታች እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም በከተማዋ እየታየ ያለው ልማት በሰዉ ኑሮና አኗኗር ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እያመጣ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
መስጠት አያጎድልም በሚል የቀረበውን ጥሪ ተቀብለው ለተባበሩ ልበ ቀና ባለሀብቶችና ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በጉልበታቸው በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገሉ ላሉ ወጣቶች በራሳቸውና በነዋሪዎች ስም ምስጋና አቅርበዋል።
በተለይም በዛሬው ዕለት በከንቲባ ፅህፈት ቤት ለቀረበው ማዕድ ማጋራት( Jospong integrated waste management plc) 15 ሚሊዮን ብር፣ አቶ ጀማል አህመድ (ሚድሮክ) 10 ሚሊዮን ብር፣ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል ቤተክርስቲያን 7 ሚሊዮን ብር፣ አቶ በላይነህ ክንዴ (BKG) 5 ሚሊዮን ብር፣ አትሌት ዮሐንስ ቢፋ 2 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር እንዲሁም አቶ ተካበ ሙሉ 500 ሺህ ብር ድጋፍ በማድረጋቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የትንሳኤ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን ፍቅሩን እስከ መስቀል የገለጸበት በመሆኑ፣ ነዋሪዎች በዓሉን ሲያከብሩ በታላቅ ፍቅርና መተሳሰብ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።
ሁሉም ዜጋ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ያለውን አጋርነት በተግባር በመግለጽ አንዱ ለሌላው የደስታ፣ የሰላምና የአብሮነት ምክንያት እንዲሆን በመመኘት በራሳቸውና በከተማ አስተዳደሩ ስም መልካም የበዓል ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።