ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላለፉት 80 ዓመታት የዕድገትና የሀገር ኩራት ምሳሌ ሆኖ ቀጥሏል

አዲስ አበባ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ ላለፉት 80 ዓመታት የዕድገት፣ የትርፋማነት እና የሀገር ኩራት ምሳሌ ሆኖ መዝለቁን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ገለፁ።

አየር መንገዱ ፈተናዎች በጽናት በማለፍ አፍሪካን ከዓለም ጋር የሚያገናኝ ቀዳሚ የአቪዬሽን ተቋም መሆኑን በተግባር ማረጋገጡንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓልን አስመልክቶ የአየር መንገዱ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ ተቋሙ ባለፋት ስምንት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ የዕድገት፣ የትርፋማነት እና የሀገር ኩራት ምሳሌ ሆኖ መዝለቁን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ የመጀመሪያ በረራውን መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም ማድረጉን ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በነበሩት ዓመታት ባስመዘገበው ተከታታይ ዕድገት በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 145 መዳረሻዎች ያሉት ግዙፍ አየር መንገድ ለመሆን መብቃቱን ተናግረዋል።

አየር መንገዱ ዘመኑ ያፈራቸውን እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖች በመጠቀም ለደንበኞቹ የላቀ አገልግሎት እያቀረበ እንደሚገኝ ጠቅሰው፥ በተለይም በተቋም ግንባታ ረገድ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት የራሱን አውሮፕላኖች ጥገና ማከናወን የሚያስችል ሙሉ አቅም የፈጠረ ሲሆን ይህም ለኩባንያው ዘላቂ ዕድገት ትልቅ መሠረት መጣሉን አመላክተዋል።

የአቪዬሽን ባለሙያዎችን ለማፍራት የራሱ አቪዬሽን አካዳሚ ያለው አየር መንገዱ፥ የአፍሪካ ትልቁን የአቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ በመገንባት በታሪኩ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ስኬት ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ ራዕዩን መሸከም የሚችል ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት እና የሥራ ሥነ-ምግባር ያለው ታታሪ ሠራተኛ በመፍጠር ረገድ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

የካርጎ የጭነት አገልግሎት አቅሙን ከማሳደጉም በላይ በርካታ ደጋፊ መሠረተ ልማቶችን ገንብቷል ብለዋል።

እነዚህ የተቀናጁ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የደንበኞችን እርካታ ታሳቢ ያደረጉ አሰራሮች አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ የገበያ ውድድር ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ እንዲቀጥልና አስተማማኝ ዕድገት እንዲያስመዘግብ አስችለውታል ነው ያሉት።

አየር መንገዱ 150 አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን የበረራ ተደራሽነቱንና ጥራቱን ይበልጥ ለማሳደግ 117 አዳዲስ አውሮፕላኖችን ለመግዛት በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ያለፉት ሰማንያ ዓመታት ለአየር መንገዱ የታታሪነት፣ የጠንክሮ መስራት እና የስኬት ዘመናት መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገጠሙትን ፈተናዎች በጽናት በማለፍ አፍሪካን ከዓለም ጋር የሚያገናኝ ቀዳሚ የአቪዬሽን ተቋም መሆኑን በተግባር ማረጋገጡን ጠቅሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም