በዓላትን ስናከብር የተቸገሩትን በማሰብና ካለን ላይ በማካፈል ሊሆን ይገባል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በዓላትን ስናከብር የተቸገሩትን በማሰብና ካለን ላይ በማካፈል ሊሆን ይገባል-ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦በዓላትን ስናከብር የተቸገሩትን በማሰብና ካለን ላይ በማካፈል ሊሆን እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ መጪው የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው እና አቅመ ደካሞች የህብረተሰብ ክፍሎች ማዕድ አጋርተዋል።
ከንቲባዋ በማዕድ ማጋራት መርሃግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ በዓላትን ስናከብር የተቸገሩትን በማሰብና ካለን ላይ በማካፈል ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ይህንን ተግባር በየዓመቱ የሚያከናውነው ዜጎች በዓላትን በደስታ እንዲያሳልፉ ለማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።
አቅመ ደካሞችንና አረጋውያንን በመደገፍ በዓልን በጋራ ማክበር የቆየው የኢትዮጵያውያን መልካም እሴት መሆኑን አንስተው፤ የከተማ አስተዳደሩ ይህንኑ በጎ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ከንቲባዋ ይህ ድጋፍ እንዲደረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለሀብቶችና ተቋማት ምስጋና አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይመር ከበደ በበኩላቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ በሰው ተኮር ስራዎች የመረዳዳት የመደጋገፍ ባህል እያሳደግን እንገኛለን ብለዋል።
በዛሬው መርሃግብር ከ233 ሺህ በላይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።