ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ሁለት ግዙፍ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ክሶችን በድል አጠናቃለች - ፍትሕ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በወራት ልዩነት ውስጥ የቀረቡባትን ሁለት ግዙፍ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ክሶች በድል ማጠናቀቋን የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጸ።  

የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የግልግል ዳኝነት መድረክ ያገኘቻቸውን ሁለት ድሎችን አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።  

በመግለጫቸውም ሀገሪቱ በተከታታይ ያገኘቻቸው እነዚህ ድሎች በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር የካሳ ክፍያ ከማዳን ባለፈ የሀገሪቱን ሉዓላዊ ጥቅም ያስጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

ፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 943/2008 በተሰጠው ስልጣን መሠረት፣ የሕዝብና የመንግስትን የፍትሐብሔር ጥቅም የማስጠበቅ፣ የፌደራል መንግስት ዋና አማካሪ የመሆን እና በዓለም አቀፍ መድረክ ሀገሪቱ ስትከሰስ የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበት አስረድተዋል።  

ሚኒስቴሩ ዓለም አቀፍ የግልግል ማዕከላት ቢሯቸውን በኢትዮጵያ እንዲከፍቱ ከማድረግ ጀምሮ በውስጥና በውጭ ባለሙያዎች የታገዘ የሪፎርም ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። 

በድል ከተጠናቀቁት ዋና ዋና ክሶች የመጀመሪያው የቱርኩ የኮንስትራክሽን ኩባንያ የሆነው Akgun Insaat Makina Sanayii ve Dis Ticaret Ltd. Sti. የተባለው አቅርቦት ከነበረው በድምሩ ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ ክስ መሆኑን ተናግረዋል።   

ኩባንያው በለገዳዲና ድሬ ግድቦች አቅራቢያ የኢንዱስትሪ ዞን ለማልማት ፈቃድ ተሰጥቶት እንደነበር አስታውሰዋል።

አካባቢው የአዲስ አበባ የንጹህ ውሃና ምንጭ በመሆኑ የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማ ሕጉ በሚያዘው መሠረት እንዲያቀርብ በተደጋጋሚ ለቀረበለት ጥያቄ ኩባንያው አጥጋቢ ምላሽ ሊሰጥ ባለመቻሉ የኢንቨስትመንት ስራው ወደ ሌላ ምቹ ቦታ እንዲዛወር አማራጭ ቀርቦለት እንደነበር ገልጸዋል።   

ኩባንያው ግን የቀረበለትን አማራጭ ባለመቀበል የኢንቨስትመንት ጥበቃ መብት ጥሰት ደርሶብኛል በሚል ክስ ማቅረቡን በማውሳት፣ የኢትዮጵያ መንግስት ለዜጎቹ ንጹህ ውሃ የማቅረብ ኃላፊነቱን መወጣቱ በግልግል ችሎቱ ታምኖበት ክሱ ውድቅ ተደርጓል ብለዋል።  

የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባር በአከባቢ ጥበቃ ዓለም አቀፍ ህግጋትን ያከበረ እና መንግሥታዊ ሃላፊነቱን እንደተወጣ የሚቆጠር መሆኑን በማመን ክሱ ውድቅ መደረጉንም ገልጸዋል።

ሁለተኛው በኔዘርላንድ የተመዘገበው ኩባንያ African Asset Finance Company Holding B.V ወይንም በተለምዶ ኢትዮ ሊዝ እየተባለ የሚጠራው ኩባንያ፣ ሀገራዊ ግዴታዎችን እንዲያከብር የተሰጡትን ማስጠንቀቂያዎች እንደ ኢንቨስትመንት መብት ጥሰት በመቁጠር ከ334 እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር በላይ ካሳ ጠይቆ እንደነበር አንስተዋል።   

በሄግ፣ ኔዘርላንድስ በተካሄደው የቃል ክርክር የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ባቀረቡት ብርቱ ክርክር በሦስቱም ገለልተኛ ዳኞች ድምፅ ክሱ ውድቅ ሆኗል።   

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ለክርክሩ ያወጣችውን ወጪና ኪሳራ ኩባንያው እንዲከፍል መወሰኑንም ተናግረዋል።   

ፍትሕ ሚኒስቴር እነዚህን ክሶች ለመከላከል ከውስጥና ከውጭ ባለሙያዎችን በማዋቀር ብርቱ የክርክር ቡድን መገንባቱን ገልጸዋል።   

ተገቢውን ፋይናንስና ማስረጃ በማሰባሰብ የክርክር አመራር መስጠቱንም ጠቅሰዋል።   

ኢትዮጵያ  የቀረቡባትን ክሶች ማሸነፏ በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት ምህዳር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይኖር ከማድረግ ባለፈ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ካሳ  እንዳትከፍልና የኢኮኖሚ ጫና ውስጥ እንዳትገባ አስችሏታል ብለዋል።

ከድሎቹ ዋና ዋና አንድምታዎች መካከልም ታዳጊ ሀገራት ለጥቅማቸው ራሳቸውን ችለው መሟገትና መርታት እንደሚችሉ ማሳየቱ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።   

በተጨማሪም ክስን እንደ ማስፈራሪያ ለሚጠቀሙ አንዳንድ ባለሀብቶች ሕግ አክባሪነትን ማስተማሩ፣ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ስምምነቶች የምታከብርና ለጤናማ ኢንቨስተሮች ምቹ መሆኗን ማረጋገጡን ለአብነት ጠቅሰዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም