በወልዲያ ከተማ ለትንሳኤ የበዓል ገበያ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል - ኢዜአ አማርኛ
በወልዲያ ከተማ ለትንሳኤ የበዓል ገበያ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል
ወልዲያ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፡- በወልዲያ ከተማ ለትንሣኤ የበዓል ገበያ ምርቶች በበቂ ሁኔታ መቅረባቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
አስተያየታቸውን ከሰጡ የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ አያሌው መላኩ ለኢዜአ እንደገለጹት ለትንሳኤ በዓል የሚያስፈልጉ ምርቶች በስፋት ለገበያ ቀርበዋል።
ለበዓሉ የእርድ እንስሳት በሰፊው መቅረባቸውን ገልጸው እርሳቸውም ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመሆን የእርድ ሰንጋ መገብየታቸውን አስረድተዋል።
ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ አለሚቱ ያዘው በበኩላቸው ለበዓሉ ዶሮ በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛታቸውንና የፋብሪካ ምርቶችንም እንደ አቅማቸው መሸመታቸውን ተናግረዋል።
ለገበያው ዋጋ መረጋጋት የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት የራሳቸው ድርሻ እንዳበረከቱ የጠቀሱት ደግሞ ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ዘውዴ በላይ ናቸው።
የሸማቾች ማህበራቱ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ እንዳስቻሉ ጠቁመው ይህም የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት እገዛ በማድረጉ ተግባሩ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲሱ ወንድሙ በበኩላቸው በዓልን ምክንያት በማድረግ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ጊዜያዊ የመገበያያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል።
የተቋቋሙት ጊዜያዊ የገበያ ማዕከላትም ሽንኩርት፣ ዶሮ፣ እንቁላልና ሌሎች ለበዓል የሚያስፈልጉ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ህብረተሰቡ በቅርበት እንዲያገኝ ማስቻላቸውን አመልክተዋል።
ስኳር፣ ዘይት፣ የዳቦ ዱቄትና ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶችን ደግሞ በህብረት ስራ ማህበራት በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብ መደረጉን አስረድተዋል።
በከተማዋ የተከፈተው "የትንሣኤ ዋዜማ የንግድና ትርዒትና ባዛር" እስከ በዓሉ ዋዜማ የሚቀጥል በመሆኑ ህብረተሰቡ ባሉት አማራጮች የሚፈልገውን መግገበያየት እንደሚችልም ጠቁመዋል።
የከተማ አስተዳደሩ የበዓል የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች በብዛት፣ በዓይነትና በጥራት ከማቅረብ ባለፈ ህገወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ስርዓት መዘርጋቱን አንስተዋል።