ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታሪካዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሕጋዊና የትውልድ አጀንዳ ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ታሪካዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ሕጋዊና ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ የሚሻ የትውልድ አጀንዳ መሆኑን የውሃ ዘርፍ ምሁራን ገለጹ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ ዘርፍ ምሁራን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉትም፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የቅንጦት ሳይሆን ትውልድና የህልውና ጉዳይ ነው።


 

በዩኒቨርሲቲው የሲቪልና የአካባቢ ምህንድስና ትምህርት ክፍል መምህር በለጠ ብርሃኑ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ስልጣኔ የዓባይ እና የቀይ ባሕር ውሃዎች የጋራ ቅኝት የሚመነጭ ድምር ውጤት ነው ብለዋል።

የዓባይ እና የቀይ ባሕር ሁለቱ ውሃዎች የቀጣናዊ፣አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሀገር ግንባታና የኢኮኖሚ ዕድገት መሰሶ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም በሕጋዊ፣ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መልክዓ-ምድራዊ ምክንያታዊነት መነፅር የሚታይ የትውልድ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም ከሕግ፣ታሪክ፣ስልጣኔ፣ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው የትውልድና የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሌላኛው በዩኒቨርሲቲው የኃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪና ዓለም አቀፍ የውሃ ተደራዳሪ ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)፤የባሕር በር ባለቤትነት በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችም የሽፍታ ግርግርን በመጠቀም ኤርትራን በማስገንጠል ሀገር የስልጣኔ መነሻዋ ከሆነው የባሕር በር ባለቤትነት እንድትርቅ መደረጉን አስታውሰዋል።

ብዝኅ የወደብ መዳረሻና የባሕር በር ባለቤት የነበረችው የኢትዮጵያ ሕጋዊ፣ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መልክዓ-ምድራዊ ጥያቄም በህዝብ ልብ ውስጥ የቆየ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ምሁራኑ በማከልም፤የኢትዮጵያ የሁለቱ ውሃዎች ጉዳይ የሀገርን ክብርና ልዕልና የማስጠበቅ ስትራቴጂክ የህዝብ አጀንዳ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ሕዳሴን በዓባይ ላይ እውን ያደረገው ይህ ትውልድም ዲፕሎማሲያዊና ሕጋዊ መርህን በመከተል የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ምላሽ ማስገኘት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታሪካዊ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም ሕጋዊና ዲፕሎማሲያዊ ምላሽ የሚሻ የትውልድ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም