ቀጥታ፡

በሰመራ ከተማ አስተዳደር የለማው ስንዴ ለአካባቢው የዳቦና ዱቄት አቅርቦት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል

ሰመራ፣ መጋቢት 30/2018(ኢዜአ)፡- በሰመራና ሎጊያ  ከተማ አስተዳደር የለማው ስንዴ ለሰመራና አካባቢው የዳቦና ዱቄት አቅርቦት  ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ።

የሰመራ ከተማ አስተዳደር በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት  የልማት ፕሮጀክቶች አስተባባሪነት በከተማው ለተገነባው  ብርሃን የዳቦና ዱቄት ፋብሪካ ግብአት የሚሆን በዱብቲ ወረዳ በ100 ሄክታር መሬት ላይ ያለማውን ስንዴ መሰብሰብ ጀምሯል።

በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በሰመራ የተገነባው ፋብሪካው መጋቢት 13 ቀን 2017 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር)፣ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውና የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አወል አርባ በተገኙበት በይፋ መመረቁ የሚታወስ ነው።

በምርት ስብሰባው ወቅት የተገኙት የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱ ሙሳ እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ የለማው የስንዴ ምርት ለሰመራና አካባቢው ዳቦና ዱቄት አቅርቦትና ገበያን ለማረጋጋት  አስተዋፅኦ እያደረገ  ነው። 


 

በቀዳማዊ እመቤት ጽህፈት ቤት የተገነባው የዳቦና ዱቄት ፋብሪካው የአካባቢውን ህብረተሰብ ችግር እየፈታ መሆኑንም ገልጸዋል።

እስካሁን ያለው የዳቦ ምርት ከሌላ ቦታ በሚመጣ ስንዴ የተጀመረ መሆኑን ገልፀው አሁን ላይ በ100 ሄክታር መሬት ላይ የለማው ስንዴ መሰበሰብ በመጀመሩ ፋብሪካው በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ ምርትን ማቅረብ የሚያስችለው መሆኑን ገልፀዋል።

የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ የአካባቢው የአየር ጠባይ የተላመደ ዘር  መገኘቱንና ይህም የፋብሪካውን የማምረት አቅም  ከፍ በማድረግ  ለአካባቢው ማህበረሰብ በተመጣጣነ ዋጋ ማቅረብ የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።


 

የፋብሪካው ዋና ስራ አሰኪያጅ አቶ ሁሴን ይመር በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ የሚያቀርበው የስንዴ ምርት ፋብሪካው     በቅርበትና በተመጣጣኝ ዋጋ  ግብአትነት እንዲያገኝ ማገዙን ጠቁመዋል።

ለፋብሪካው  ምርቶች  በበቂ ሁኔታና በጥራት መቅረባቸው የማህበረሰቡን ፍላጎት ለማርካት የራሱ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል።

ፋብሪካው በሰመራና ሎጊያ ከተማ እንዲሁም በአካባቢው ያለውን የዳቦና የዱቄት እጥረት በማቃለል ረገድ  ሚናው ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም