በጎንደር ከተማ የሸማቾች ማህበራትን በመደገፍ የተረጋጋ የበዓል ግብይት ለመፍጠር ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ የሸማቾች ማህበራትን በመደገፍ የተረጋጋ የበዓል ግብይት ለመፍጠር ትኩረት ተደርጓል
ጎንደር፤ መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦በጎንደር ከተማ የሸማቾች መሰረታዊ ማህበራትን በመደገፍ የተረጋጋ የበዓል ግብይት ለመፍጠር ትኩረት መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡
በመምሪያው የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ ቡድን መሪ አቶ አወቀ ሀጎስ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የሸማቾች መሰረታዊ ማህበራትን በመደገፍ የተረጋጋ የበዓል ግብይት ለመፍጠር በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በክፍለ ከተሞች በትላልቅ ድንኳኖች በመጠቀም የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶችን በዓይነት፣ በብዛትና በጥራት ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ይህም አምራቾችንና አቅራቢዎችን በቀጥታ ከሸማቹ ማህብረሰብ ጋር በማገናኘት በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገበያዩ እድልን የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በአምራች ኢንዱስትሪዎች በቅርቡ ስራ በጀመረው የ2ኛ ደረጃ የግብይት ማዕከል ውስጥ ከ40 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይትና የዳቦ ዱቄት የሚያቀርቡበት ሁኔታ ተመቻችቷል ብለዋል።
በከተማው የሚገኙ 22 መሰረታዊ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራትም ቀድመው ለበዓል የሚሆን ምርት ካለበት ቦታ በማስገባት አሁን ላይ ለህብረተሰቡ ማቅረባቸውን አስረድተዋል።
በዶሮ እርባታና በእንቁላል ምርት ስራ ላይ የተሰማሩ 13 አምራችና አቅራቢ ድርጅቶችም ለበዓል ገበያው ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንቁላሎችና ከ2 ሺህ በላይ ዶሮዎችን ለህብረተሰቡ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል፡፡
በከተማው የሚገኙ ከ200 በላይ የስጋ ቤቶችም በዓሉን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ እንዳያደርጉ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም የገበያ አረጋጊ ግብረ ሃይል በማቋቋም በመከዘን የምርት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት በሚፈጥሩ ህገወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ገልጸዋል።
የራስ ዳሽን የሸማቾች ህብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ አድና አለምዬ እንዳሉት፥ ዩኒየኑ ለበዓል ገበያ የሚሆኑ ምርቶችን ቀድሞ ካለበት ቦታ በማስመጣት ለህብረተሰቡ ማቅረቡን ገልጸዋል።
የምግብ ዘይት፣ ስኳር፣ የዳቦ ዱቄት፣ ፓስታና ማኮሮኒ፣ ሩዝ፣ ጤፍና ሌሎች ምርቶችን በገበያ ካለው እስከ 20 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ለህብረተሰቡ ማቅረቡን ተናግረዋል።