ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ለትንሳኤ በዓል ፍጆታ የሚውሉ መሰረታዊ ምርቶች በተሻለ ሁኔታ እንዲቀርቡ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣መጋቢት 30/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ለዘንድሮ የትንሳኤ በዓል ፍጆታ የሚውሉ መሰረታዊ ምርቶች በተሻለ ሁኔታ ለገበያ እንዲቀርቡ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ንግድ ቢሮ የገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ጉቱ ተመስጌን ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ለዘንድሮው የትንሳኤ በዓል የተሻለ የምርት አቅርቦት እንዲኖርና ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ከባለድርሻ አካላት ጋር እቅድ በማውጣት የተለያዩ ተግባራት እየተሰሩ ነው።

በክልሉ በቂ ምርት ያለበት አከባቢና የዋጋ ሁኔታን በማጥናት ወደ ሌሎች የምርት አቅርቦት እጥረት ያለበት ቦታዎች እንዲደርስና የገበያ ትስስር ለመፍጠር ሰፊ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።

በተለይም አትክልትና ፍራፍሬ፣የቁም እንስሳት፣ እንቁላልና ዶሮ እንዲሁም ሌሎች በስፋት የሚቀርቡ የበዓል ፍጆታዎች መሆናቸውን ገልጸው፤ ዘይትና ስኳር ደግሞ በማህበራትና ዩኒየኖች በኩል እንዲቀርቡ ተደርገዋል ብለዋል።

ምርቶቹም በክልሉ ባሉት 775 የሰንበት ገበያዎችና በዐውደ ርዕይና ባዛሮች ላይ እየቀረቡ እንዳሉ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣በተለይም ሁለት ቀናት ብቻ የነበረው የሰንበት ገበያ ለበዓሉ ለ10 ተከታታይ ቃናት እንዲከፈት ተደርጓል ብለዋል።

ለበዓል ፍጆታ የሚውሉ በቂ መሰረታዊ ምርት እንዳለ የተናገሩት አቶ ጉቱ፣ አቅርቦቱን ለማሳለጥና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የክትትልና ቁጥጥር ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም