ቀጥታ፡

የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓቱ ስራ ፈላጊዎችን ከቀጣሪዎች ጋር በማገናኘት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ስራ ፈላጊዎችን ከቀጣሪዎች ጋር በማገናኘት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ።

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የዲጂታል ሥርዓቱን ተደራሽነት ከማስፋቱም በላይ በፋይናንስ ቴክኖሎጂ አማካይነት አዳዲስ የሥራ አማራጮች እንዲፈጠሩ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የስራ ገበያ መረጃ ሥርዓት የሰው ኃይል ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም የተዘጋጀ ዲጂታል መድረክ ነው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የሥራ ፈላጊዎች ቁጥር እና በየዘርፉ ያሉ ክፍት የሥራ መደቦችን በአንድ ማዕከል የማሰባሰብና የሰው ኃይሉን በዘመናዊ መረጃና ክህሎት በመገንባት ለዓለም አቀፍ ገበያ ጭምር ብቁ ማድረግ ከገበያ መረጃ ስርዓቱ ዓላማዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ስራ ፈላጊዎችን ከቀጣሪዎች ጋር በማገናኘት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

ስርዓቱ ተግባራዊ ከተደረገ ከአራት ዓመታት በላይ እንደሆነው አንስተው፤ በዚህም ለአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊየን ዜጎች በውጭ ሀገራት ስራ መሰማራታቸውን አስታውቀዋል፡።

በሀገር አቀፍ ደረጃም 45 ሺህ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ስራ ፈላጊ ወጣቶች ስራ ቅጥር እንዲፈጽሙ ስርዓቱ አስቻይ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፣ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የዲጂታል ሥርዓቱን ተደራሽነት ከማስፋቱም በላይ በፋይናንሻል ቴክኖሎጂ አማካይነት አዳዲስ የሥራ አማራጮች እንዲፈጠሩ ረድቷል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 የዲጂታል ፕላትፎርምን በመጠቀም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን አንስተው፤ ይህንንም በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በአጠቃላይ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓቱ በውጭ ሀገራት የርቀትና የፍሪላንስ የስራ አማራጮች እንዲሁም በአገር ውስጥ በቴክኖሎጂ የታገዙ የስራ አማራጮች ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች ቁጥር እንዲያድግ እያስቻለ መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም