የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች በሀገራቸው የዴሞክራሲ ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉበት የዜግነት ክብር መገለጫ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች በሀገራቸው የዴሞክራሲ ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉበት የዜግነት ክብር መገለጫ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ዜጎች በሀገራቸው የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉበት የዜግነት ክብር መገለጫ መሆኑን አባትና እናት አርበኞች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮውን ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ መጋቢት 28/2018 ዓ.ም ሲያካሂድ ቆይቷል።
በተጨማሪም ቦርዱ የመራጮችን ምዝገባ ሁለት የበዓል ቀናትን ሳይጨምር እስከ ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም አራዝሟል።
በቦርዱ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ደግሞ ድምጽ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
በመሆኑም መራጮች በዲጂታል "ምርጫዬ" መተግበሪያና በየምርጫ ጣቢያዎች በአካል በመገኘት ድምፅ መስጠት የሚያስቻለቸውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 47 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎችን በማስመዝገብ በመገናኛ ብዙኅን አማካኝነት የፖሊሲ አማራጭ ሃሳባቸውን ለህዝብ በማስተዋወቅ ላይ ናቸው።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አባላት ለኢዜአ እንዳሉት፤ ምርጫ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ባህል በመገንባት የሀገር ፍቅርና ክብር የሚገለፅበት የዜጎች የጋራ መድረክ ነው ብለዋል።
አባት አርበኛ ባሻ ሽመልስ ወልደ-ተክሌ፤ በኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን ካርድ መውሰዳቸውን አስታውቀዋል።
ዜጎችም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰጠው ተጨማሪ የድምፅ መስጫ ካርድ ማውጫ ጊዜን በመጠቀም ካርድ መውሰድ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ ምርጫ የኢትዮጵያን የዴሞከራሲ ባህል በመገንባት የዜግነት ክብር መገለጫ ወሳኝ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም ዜጎች ይበጀናል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት ከወዲሁ በመዘጋጀት ለሀገራቸው ያላቸውን ክብር ማሳየት እንደሚኖርባቸው አንስተዋል።
ሌላኛው አባት አርበኛ ኮሎኔል አያሌው በላይ፤ ምርጫ የዜግነት ክብር መገለጫና ሕገ-መንግስታዊ የመምረጥና መመረጥ መብት ማረጋገጫ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ የሀገርን የዴሞክራሲ ባህል ለመገንባት አንዱ መሳሪያ ነው ያሉት አባት አርበኛ ኮሎኔል አያሌው፤ የሀገርን የዴሞክራሲ ባህል ለማጠናከር የምርጫ ተሳትፎ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው አስገንዝበዋል።
በዚህም በምርጫ ሂደት ድምፅ ለመስጠት ዕድሜው የሚፈቅድለት ሁሉም ዜጋ የምርጫ ካርድ በማውጣት ይበጀኛል የሚለውን ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀት እንዳለበት አስረድተዋል።
እናት አርበኛ አልማዝ አንበርብር በበኩላቸው፤ ምርጫ የሀገርን ልማትና ዕድገት ለማስቀጠል ዜጎች በአደባባይ የሚሳተፉበት የጋራ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
ሁሉም ዜጋ ድምፅ መስጠት የሚያስችለውን ካርድ በማውጣት ለሀገሩ ያለውን ክብር በምርጫ ተሳትፎ ማሳየት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ዜጎች የመምረጥና መመረጥ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ይበጀናል ለሚሉት ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።