የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30 /2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ አራት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ከቀኑ 10 ሰዓት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ካደረጋቸው 24 ጨዋታዎች መካከል ሰባቱን ሲያሸንፍ፤ በ10 ሽንፈት አስተናግዷል። በሰባት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በ24ቱ ጨዋታዎች ላይ 18 ጎሎችን ሲያስቆጥር 21 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
የ16 ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ28 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ 25 ጨዋታዎችን አድርጎ በዘጠኙ አሸንፎ በአምስቱ ተሸንፎ በቀሪ 11 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 19 ግቦችን ሲያስቆጥር 13 ጎሎችን አስተናግዷል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ38 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
በ25ኛ ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕናን 2 ለ 1 ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል። ካሸነፈ ከወራጅ ቀጠና ይወጣል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ25ኛ ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል። ቡድኑ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከሸገር ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ ቡና እስከ አሁን በሊጉ 24 ጨዋታዎችን አድርጎ 10 ጊዜ ሲያሸንፍ፤ በዘጠኙ ተሸንፏል። በቀሪ አምስት ጨዋታዎች ነጥብ ጥሏል። 24 ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ 24 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ35 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ሸገር ከተማ በበኩሉ በሊጉ ባከናወናቸው 25 ጨዋታዎች በስድስቱ ሲያሸንፍ ሰባት ጊዜ ሽንፈት አጋጥሞታል። በቀሪ 12 ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ላይ 22 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 23 ግቦች ተቆጥረውበታል።
አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በ30 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ቡና ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታል።
ተጋጣሚው ሸገር ከተማ ድል ከቀናው በ25ኛ ሳምንት በአርባምንጭ ከተማ ካስተናገደው የ2 ለ 1 ሽንፈት በኋላ ወደ አሸናፊነት ይመለሳል።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመቀሌ 70 እንደርታ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
የ2016 ዓ.ም የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ30 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። መቀሌ 70 እንደርታ በ23 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
በ25ኛ ሳምንት ከወላይታ ድቻ ያለ ግብ አቻ የተለያየው ንግድ ባንክ ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።
ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ያላሸነፈው መቀሌ 70 እንደርታ ጨዋታው ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ትግል ወሳኝ የሚባል ነው።
ምድረ ገነት ሽሬ ከድሬዳዋ ከተማ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከድል የራቀው ምድረ ገነት ሽሬ በ28 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ይገኛል።
ድሬዳዋ ከተማ በ29 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት የሊጉ ጨዋታዎች አላሸነፈም።
ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታሉ።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት እስከ ሚያዝያ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
ሲዳማ ቡና በ48 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
አቤል ያለው ከሲዳማ ቡና በ11 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ይገኛል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ በ10 ጎሎች ይከተላል።