የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዩራጓይ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዩራጓይ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2018 (ኢዜአ)፦ የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ያዘጋጀው የ"UEFA Frendship Cup" ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ውድድር በቱርክዬ ከመጋቢት 28 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ እየተካሄደ ይገኛል።
በዚህ ውድድር ላይ ከተለያዩ አህጉራት የተውጣጡ ሀገራት የሚሳተፉ ሲሆን፤ የኢትየጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር ጋር በፈጠረው ግንኙነት ከአፍሪካ ከሚሳተፉ ሁለት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆን ችላለች።
በዚህም የኢትዮጵያ ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ይሳተፋል።
በአሰልጣኝ ለሜቻ ግርማ የሚመራው ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ቀን 5 ሰዓት ከ30 ላይ ከዩራጓይ ጋር የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደርጋል።
አሰልጣኝ ለሜቻ ለ22 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ቡድኑ በአዲስ አበባ ዝግጅቱን ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፤ ከትናንት በስቲያ ቱርክዬ ደርሷል።
ብሔራዊ ቡድኑ ከጨዋታው በፊት በቱርክዬ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የልምምድ ሜዳ ልምምዱን አከናውኗል።
በ"UEFA Frendship Cup" ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ውድድርላይ አስተናጋጇ ቱርክዬን ጨምሮ ኢትዮጵያ፣ ኖርዌይ፣ ኡዝቤኪስታን፣ ኮስታሪካ፣ ፓራጓይ፣ ዩራጓይ እና ሞሮኮ ተሳታፊ ናቸው።
ኢትዮጵያ ከዩራጓይ በተጨማሪ ከኖርዌይ እና ኮስታሪካ ጋር ጨዋታዋን ታደርጋለች።
የወዳጅነት ስፖርታዊ ሁነቱ ከውድድር ባለፈ በአህጉራት መካከል ያለውን የእግር ኳስ ልማት ትብብርን ማጠናከር እና የልምድ ልውውጥ ማድረግን ያለመ ነው።
በተጨማሪም የታዳጊ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ምልመላ የሚደረግ ሲሆን፤ ይህም ለኢትዮጵያ ተጫዋቾች መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል።
የ"UEFA Frendship Cup" ከ18 ዓመት በታች ሴቶች ውድድር እስከ ሚያዝያ 10 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።