ቀጥታ፡

በሻምፒዮንስ ሊጉ ፒኤስጂ ከሊቨርፑል ባርሴሎና ከአትሌቲኮ ማድሪድ የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ተጠባቂ ናቸው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 30/2018(ኢዜአ):- በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዛሬ ሁለት የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ምሽት አራት ሰዓት ላይ ፒኤስጂ ሊቨርፑልን በፓርክ ደ ፕሪንስ ያስተናግዳል።

የፈረንሳዩ ፒኤስጂ በጥሎ ማለፉ ቼልሲን በማሸነፍ ስምንት ውስጥ ገብቷል።  ተጋጣሚው ሊቨርፑል ጋላታሳራይን በመርታት ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል።

ሁለቱ ቡድኖች በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለአምስተኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም እርስ በእርስ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ አሸንፈዋል።

ቡድኖቹ በአራቱ ጨዋታዎች ላይ በተመሳሳይ አምስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

እ.አ.አ 2024/25 በጥሎ ማለፉ ተገናኝተው ፒኤስጂ በድምር ውጤት በማሸነፍ ሩብ ፍጻሜ መግባቱ የሚታወስ ነው።

የፓሪሱ ክለብ የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ነው።

ሊቨርፑል የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን ስድስት ጊዜ አንስቷል።

ጨዋታው ለተመልካች ሳቢ እና ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል።

 

ሌላኛው ጨዋታ ምሽት አራት ሰዓት ላይ ባርሴሎና እና አትሌቲኮ ማድሪድን በካምፕ ኑ ስታዲየም ያገናኛል።

ሁለቱም ቡድኖች ወደ ሩብ ፍጻሜ የገቡት የእንግሊዝ ክለቦችን በመርታት ነው።

ባርሴሎና ኒውካስትል ዩናይትድን፣ አትሌቲኮ ማድሪድ ቶተንሃም ሆትስፐርስን አሸንፈዋል።

ቡድኖቹ በሻምፒዮንስ ሊጉ ለአምስተኛ ጊዜ ይገናኛሉ።

ከዚህ በፊት ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች አትሌቲኮ ማድሪድን ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ባርሴሎና አንድ ጊዜ ድል ቀንቶታል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

በአራቱ ጨዋታዎች ላይ አትሌቲኮ ማድሪድ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር ባርሴሎና ሶስት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ሁለቱ ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ በውድድሩ ላይ የተገናኙት እ.አ.አ 2015/16 ነበር።

በወቅቱ በሩብ ፍጻሜ ተገናኝተው አትሌቲኮ ማድሪድ በድምር ውጤት 3 ለ 2 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ ማለፉ አይዘነጋም።
 

ከ10 ዓመታት በኋላ በድጋሚ በሩብ ፍጻሜው ተገናኝተዋል። ጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም