የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ታዳጊ ብሔራዊ ቡድን በሞሮኮ በሚካሄደው 16ኛው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ዝግጅት ማድረጉን ቀጥሏል።
ቡድኑ ላለፉት ቀናት 30 ተጫዋቾችን በመያዝ በቀን ሁለት ጊዜ ዝግጅቱን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት ደግሞ ረፋድ ላይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ልምምዱን አከናውኗል።
ከዛሬው ልምምድ በኋላም ስብስቡን ወደ 27 መቀነሱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
ከዋና አሰልጣኝ ቤንጃሚን ዚመር እና ረዳቶቻቸው በተጨማሪ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ አማካሪ አምሳሉ ፋንታሁን ከአሜሪካ ዛሬ አዲስ አበባ ገብተው ቡድኑን መቀላቀላቸውን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በሕዳር ወር 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሶስተኛ መውጣቱን ተከትሎ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ የሚታወስ ነው።
16ኛው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ከሚያዝያ 17 እስከ ግንቦት 7 ቀን 2018 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።
በውድድሩ ላይ 16 ሀገራት ይሳተፋሉ።
በአፍሪካ ዋንጫው ከሚሳተፉ 16 ሀገራት መካከል የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ 10 ሀገራት በጥቅምት እና ሕዳር ወር 2019 ዓ.ም በኳታር ለሚካሄደው 20ኛው የፊፋ ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ያልፋሉ።