የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለአምራች ኃይል ግንባታ ያለው ፋይዳ የላቀ ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለአምራች ኃይል ግንባታ ያለው ፋይዳ የላቀ ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፦ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለአምራች ኃይል ግንባታ ያለው ፋይዳ የላቀ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
የምግብ እና ስርዓተ ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ስኬት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፤ ይህም በተለይ ለጀርባ አጥንት ለሆነው አምራች እና ተመራማሪ ኃይል ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ የላቀ መሆኑን አመልክተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በበይነ መረብ ባካሄዱት ውይይት፤ የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን፣ የሰቆጣ ቃል ኪዳን፣ የጤና መድህን፣ የጽዱ ኢትዮጵያ የማስፋፊያ አድቮኬሲ እና የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማሻሻያ የ2018 ዓ.ም የስድስት ወራት ዕቅድ አፈፃፀምን ገምግመዋል።
በዚሁ መድረክ በፌዴራል ደረጃ የተከለሰውን የምግብ ስርዓት ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ የጸደቀ ሲሆን፣ በእቅዱ የተመለከቱ ቁልፍ ተግባራት በሁሉም የሴክተር መስሪያ ቤቶች እና የክልል ቢሮዎች ተካተው ተግባራዊ እንዲሆኑም መመሪያ ሰጥተዋል።
የሰቆጣ ቃል ኪዳን ትግበራን በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሷን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የ15 ዓመቱ ፍኖተ ካርታ አካል የሆነውን የመጨረሻውን የአምስት ዓመት የማስፋት ምዕራፍ (ከ2019 እስከ 2023 ዓ.ም) የትግበራ እቅድ መጽደቁን ይፋ አድርገዋል።
በዚህም የመቀንጨር እና ሌሎች የስርዓተ ምግብ ችግሮችን በፍጥነት ለመቀነስ እስከ አሁን የተገኙ ልምዶችን በመቀመር ማህበረሰቡን በባለቤትነት ማሳተፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የፌዴራል የምግብ ስርዓት እና ስርዓተ ምግብ ምክር ቤትን ለማቋቋም በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ የባለድርሻ አካላት ግብዓት ተካቶበት ወደ ቀጣይ አፈጻጸም እንዲሸጋገር አቅጣጫ ተቀምጧል።
የጤና መድህን አገልግሎትን ይበልጥ ለማጠናከርም በክልል ደረጃ ጠንካራ አስፈጻሚ አካላትን ማደራጀትና በያዝነው ዓመት የፌዴራል ቋት (Pool) መመስረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ስምምነት ላይ መደረሱንም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።
የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ውጤታማነትን ለማስቀጠልም፣ ዜጎች እንደ መክፈል አቅማቸው መዋጮ የሚያደርጉበት አሰራር መጠናከር እንዳለበትም አመልክተዋል።
ፕሮግራሙ ያለው ለሌለው የሚደጋገፍበት ወሳኝ ስርአት በመሆኑም፣ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የጽዱ ኢትዮጵያ የማስፋፊያ አድቮኬሲ እና የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማሻሻያ ፍኖተ ካርታን በተመለከተ፣ ቀጣይ የ5 ዓመታት ትግበራዎች በከፍተኛ ህዝባዊ ንቅናቄ እንዲመሩ መወሰኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም በፌዴራል እና በክልል ደረጃ ለፕሮግራሙ ልዩ ትኩረት በመስጠት በቂ በጀት እንዲመደብና ከተለያዩ ምንጮች የሀብት ማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።