የትንሳዔ በዓልን ተከትሎ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች አቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በቂ ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የትንሳዔ በዓልን ተከትሎ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች አቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በቂ ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፦ የትንሳዔ በዓልን ተከትሎ መሠረታዊና የበዓል የፍጆታ ምርቶች አቅርቦት እጥረት እና የዋጋ ንረት እንዳይከሰት በቂ የዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።
ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ ለትንሳዔ በዓል የተከናወኑ የገበያ ማረጋጋት ስራዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም የበዓልና መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረትና እጥረት እንዳይከሰት ለወራት ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል ብለዋል።
በዚህም ከተማ አስተዳደሩ ለበዓል የእርድ እንስሳትን ጨምሮ የኢንዱስትሪ እና የግብርና ምርቶች በስፋት ወደ ከተማዋ እንዲገቡ ማድረጉን ገልጸው፤ ትስስሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ምርቶቹ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የግብርና ምርቶች ገበያ ማዕከላት፣ በባዛሮች፣ በሰንበት ገበያዎች፣ በሸማች ማህበራትና ሌሎች የገበያ ማዕከላት እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ከተማ አስተዳደሩ በመካከለኛው ምስራቅ ያለውን ጦርነት ተከትሎ የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት በምርቶች አቅርቦት ላይ ጫና እንዳያሳደር የተለያዩ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈም ተናግረዋል፡፡
በዚህም በተለይ የበዓል ምርት ይዘው ለሚገቡ ተሽከርካሪዎች ቅድሚያ ነዳጅ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በመሆኑም ህብረተሰቡ በከተማዋ በሚገኙ የገበያ ማዕከላት፣ ባዛሮች፣ በሰንበት ገበያዎች፣ በሸማች ማህበራትና ሌሎች የገበያ ማዕከላት ምርቶቹን በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያገኝ ነው የተናገሩት።