በክልሉ በበልግ አዝመራ ከ415 ሺህ ሔክታር በላይ ማሳ እየለማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በበልግ አዝመራ ከ415 ሺህ ሔክታር በላይ ማሳ እየለማ ነው
ቦንጋ፤ መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በዘንድሮው የበልግ ወቅት ከ415 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት እየለማ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው በሰጡት መግለጫ፤ በዘንድሮው የበልግ ወቅት በዋና ዋና ሰብሎች ብቻ ከ415 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት በማልማት ከ16 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው።
ለዚህም የአፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር መቅረቡን ገልጸው፤ የድጋፍና ክትትል ሥራውም በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ለማልማት ከታቀደው ውስጥ እስካሁን 373 ሺህ 475 ሔክታሩ መታረሱንና 126 ሺህ ሔክታሩ ደግሞ በዘር መሸፈኑን አብራርተዋል።
በአጠቃላይ ከሚለማው ውስጥም ከ124 ሺህ ሔክታር የሚልቀውን በክላስተር ለማልማት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በተመለከተ፤ በክልሉ ከለማው 5 ሺህ 700 ሔክታር ማሳ ከ2 ሺህ ሔክታር ከሚበልጠው ማሳ ላይ የነበረው ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
በመስኖ ከለማውና በአትክልት፣ በፍራፍሬ እንዲሁም በሌሎች የሆርቲካልቸር ሰብሎች ከተሸፈነው ከ51 ሺህ ሔክታር በላይ መሬት 11 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ጠቁመው፤ እስካሁን 9 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል።
አርሶ አደሩ አሁን ያለውን ምቹ የአየር ሁኔታ ተጠቅሞ የእርሻ ሥራውን በወቅቱ እንዲያከናውን አሳስበዋል።