ቀጥታ፡

ህገ-ወጥ የእንስሳት እርድ እና ሥጋ ዝውውርን ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ ከበዓላት ጋር ተያይዞ የሚፈጸም ህገ-ወጥ የእንስሳት እርድ እና ሥጋ ዝውውርን ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል።

የአዲስ አበባ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት፣ የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር እና የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የትንሳኤ በዓል ዝግጅት አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ፀጋ ለማ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ህገ ወጥ የእንስሳት እርድና ሥጋ ዝውውርን ለመቆጣጠር የዝግጅት ስራዎች ተጠናቀዋል፡፡

በበዓል ወቅት የሚቀርብ ሥጋ ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን የኮሚሽኑ የህክምና ባለሙያዎች ጥራትና ደህንነቱን የማረጋገጥ ተግባር እንደሚከናውኑ ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አባባ ቄራዎች ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረሚካኤል በበኩላቸው፤ ድርጅቱ የእርድ ክፍል ማስፋፋት፣ የውሃ ጉድጓድ እንዲሁም አዳዲስ 10 ተሸከርካሪዎችን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በተለይም ድርጅቱ ህገ-ወጥ እርድን ለመከላከል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ እንዳሉት፤ ህገ-ወጥ የእንስሳት ዝውውርንና እርድን ለመከላከል ኮሚቴ በማዋቀር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ሀላፊ የምስራች ግርማ፤ ባለስልጣኑ አንድ ተቋም በህገ ወጥ መንገድ የከብት እርድ ሲያከናውን ከተገኘ ከ15 ሺህ ብር ቅጣት ጀምሮ እንደ ጥፋቱ ደረጃ የማሸግ እርምጃ እንደሚወስድ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም