ቀጥታ፡

አዋጁ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ጉዞን ለማፋጠን ትልቅ ዐቅም ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 29/2018 (ኢዜአ)፡- የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አዋጅ የዘርፉን ትራንስፎርሜሽንና ምርታማነት ለማሳደግ ትልቅ ዐቅም እንደሚፈጥር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ 14ኛ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።



 
በምክር ቤቱ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ "የባለብዙ ተዋንያን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ" ላይ የውሳኔ ሐሳብ ካቀረበ በኋላ ምክር ቤቱ መርምሮ አዋጁን ቁጥር 1411/2018 አድርጎ አጽድቋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ የውሳኔ ሐሳቡን ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፤ አዋጁ በመንግሥት ብቻ ተወስኖ የቆየውን የግብርና ኤክስቴንሽን አገልግሎት ወደ ባለብዙ ተዋንያን ሥርዓት የሚቀይር ነው።

ይህም በዘርፉ የግል ባለሀብቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ሌሎች አካላት በሕጋዊ መንገድ እንዲሳተፉ በር ይከፍታል ብለዋል።

አዋጁ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና ዲጂታል አሠራሮችን ለአርሶአደሩ ተደራሽ ማድረግን ጨምሮ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ተደራሽነትን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድግም ተናግረዋል፡፡ 

በተጨማሪም አገልግሎት ሰጪዎች በብቃት ማረጋገጫና በምዝገባ ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፉ በማድረግ ፍትሐዊና ጥራት ያለው አገልግሎት ማረጋገጥ ያስችላል ነው ያሉት።


 

የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፤ አዋጁ ሀገር በቀል ዕውቀትን ከሳይንሳዊ መንገድ ጋር በማዳበር የግብርና ትራንስፎርሜሽኑን ለማሳለጥ ትልቅ ዐቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም